ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንኳን ደስ አለዎ---ዓለም አቀፍ ተቋማትና የአገራት መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንኳን ደስ አለዎ---ዓለም አቀፍ ተቋማትና የአገራት መሪዎች

ጥቅምት 2/2012 ዓለም አቀፍ ተቋማትና የአገራት መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ለ20 አመት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ2019 የኖቤል የሰላም አሸናፊ መሆናቸው ትናንት ተገልጿል። ይህን ተከትሎም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአገራት መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትዬሬዝ "በአፍሪካ በአሁኑ ሰአት ጠንካራ የተስፋ ነፋስ እየነፈሰ ይገኛል ለዚህም ምክንያቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው" በማለት ዶክተር አብይ የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸው ራዕይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለታሪካዊ የሰላም ስምምነት እንዲበቁ አድርጓቸዋልም ብለዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማትም ከየትኛው ጊዜ በላይ አገልጋይና ታታሪ መሪ በሚፈልግበት ወቅት "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሰላምን ለማምጣት ያደረጓቸው ጥረቶች ለዓለም ተስፋን የሰጡ ናቸው" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ሚ ፌዴሪካ ሞግሄሪኒ "ለውድ ጓደኛዬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ስለሆንክ እንኳን ደስ ያለዎት" የሚል የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል። "ሽልማቱ ለወደፊቱ ተስፋና ብርታት ይሆናቸው ዘንድ ለታላቁ የአፍሪካ አህጉር የተሰጠ ነው፤ ሸልማቱ ያለመታከት ሰላምን ለመገንባት በመሳሪያ ሳይሆን በውይይት ለሚያምኑ ሰዎች ምሳሌ የሚሆን ነው" ብለዋል። የሰብአዊ መብት ተቋም ሂዩማን ራይትስ ወች የአውሮፓ ሚዲያ ዳይሬክተር አንድሪው ስትሮህሌንም የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈው "ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ላደረጉት ስምምነትና በአገራቸው ላመጧቸው ለውጦች አውቅና የሰጠ ነው" ብለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ማድረጋቸውም ከሰሯቸው ስራዎች በዋነኛነት እንደሚጠቀስና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቀጣይ ሌሎች ለውጦችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል። የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን ገልጸዋል። የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ መሐመድ፣ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ፣ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አላዎት መልዕክት ያስተላለፉ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ናቸው። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ ማስ፣ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ የዓለም አገራት መሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅና የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ የሆነችው ኢቫንካ ትራምፕ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፋለች። በተጨማሪም የዚምባቡዌ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ፓርቲ (ኤምዲሲ) ፕሬዚዳንት ኔልሰን ቻሚሳና የዩጋንዳው ተዋቂ ሙዚቀኛና ፖለቲከኛ ቦቢ ዋይን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺህ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ። በአጠቃላይ በዘንድው ውድድሩ 301 እጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።