ኢህአዴግ ያሰበው ውህደት በዜጎች አብሮ የመኖር እሴት ላይ ተጨማሪ ዋጋ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ ያሰበው ውህደት በዜጎች አብሮ የመኖር እሴት ላይ ተጨማሪ ዋጋ ይኖረዋል
ጥቅምት 1/2012 ኢህአዴግ ሊያደርገው ያሰበው ውህደት በዜጎች አብሮ የመኖር እሴትና ኢትዮጵያዊነትን በማጠናከር በኩል ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ ታዬ ቦጋለ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ "ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/" አራት እህት ድርጅቶች የተፈጠረ ግንባር መሆኑ ይታወቃል። ግንባሩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ቤጉህዴፓ/፣ የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ /ሐብሊ/፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋህዴን/፣ የሶማሌ ህዝቦች ዴሞራሲያዊ ፓርቲ /ሶህዴፓ/ እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ የተባሉ አምስት ፓርቲዎች ደግሞ በአጋርነት ይዟል። ሆኖም ይህንን በግንባርና አጋርነት የሚገኘውን ፓርቲ በመተው አንድ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት ታስቧል። ሀዋሳ ላይ በተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ግንባሩን ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል። ይህንን የፓርቲውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የታሪክ መምህሩ ታዬ ቦጋለ ለኢዜአ እንዳሉት ውህደቱ እውን ከሆነ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን አንዱን ብሔር ከሌላው አብልጦ የማየት እሳቤ የሚያስወግድ ይሆናል። በዜጎች አብሮ የመኖር እሴትና ኢትዮጵያዊነትን በማጠናከር በኩል አወንታዊ ሚና እንዳለውና ሁሉም ዜጋ በአገሪቱ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆንም ያግዛል ነው ያሉት። የኢህአዴግ የድርጅቶች አወቃቀር ከስያሜው ጀምሮ እሀትማማች ፓርቲና አጋር ፓርቲ ብሎ መለየት በራሱ ከፋፋይ ነበር ብለዋል መምህር ታዬ። ፓርቲው አሁን ሊተገበር ያሰበው ውህደት የመንግስትን አብሮ የመኖር እሴት ለማጠናከር የያዘውን አቋም ያሳየም ነው ብለዋል። ለአጋር ድርጅቶችም በአገሪቷ ፓለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደረግ እንደሆነም ጠቁመዋል። ላለፉት በርካታ ዓመታት ከአገር ይልቅ ብሔር ቀድሞ የታየበትና አንዱን ብሔር ከሌላው አብልጦ የማየት እሳቤ የተንሰራፋበት ነበርም ነው ያሉት። ይህ ደግሞ ማህበረሰብ ውስጥ የነበረውን አብሮ የመኖር እሴት የከፋፋለና ቁርሾ የፈጠረ በአገራዊ አንድነት ላይም ጥላሸትን የቀባ ነበር ብለዋል። በቀጣይ ሊፈጠር የታሰበው ውህደት ግን የነበረው የመገለል እሳቤ አጥፍቶ በአገራዊ ውሳኔ ላይ ሁሉም ብሔር እኩል ተሳታፊ አንዲሆን ያግዛል ብለዋል። በአገሪቱ ለዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ መስፋትና ለፌዴራል ስርዓቱ መጠናከር በጎ አስተዋዕኦ ያበረክታል ነው ያሉት። ኢህአዴግ የውህደት ጉዞውን በማፋጠን ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሳሌነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል።