ቀጥታ፡

የኖቤል ሽልማቱ ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተስፋ ያመላከተ ነው-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

መስከረም 30/2012 የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት ለስራዎቻቸው ዕውቅና እንዲሁም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተስፋ ያመላከተ መሆኑን ገለጹ። ፕሬዚዳንቷ ሽልማቱን አስመልክቶ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ "የእንኳን ደስ ያላችሁ" መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ሰላም ይቅርታና ፍቅርን ከማቀንቀን አቋርጠው  አያውቁም ያሉት ፕሬዚዳንቷ በዚህም አስፈሪ የነበረውን የፖለቲካ ፍጥጫ ማርገብ መቻላቸውን አንስተዋል። ለረጅም ዓመታት በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው ገብተው መስራት እንዲችሉ ምቹ ምህዳር ከመፍጠር ጀምሮ ታሪካዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግና ስህተቶችን በማረም በኩልም ትልቅ ስራ ሰርተዋል ነው ያሉት። ለ20 ዓመታት በግጭት የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራን ውጥረት ወደ ሰላም በመቀየርና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በማምጣትም የተዋጣለት ተግባር አከናውነዋል። ''የሽልማቱ ዋና ትርጉም ለዘላቂ ስራዎቻቸው ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና የተሰጠበት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተስፋ ያመላከተበት ነው'' ብለዋል። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ከሰራን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ካለፈው ታሪኮቻችን ማየት እንችላለን ያሉት ፕሬዚዳንቷ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ ጊዜ አገሪቷ የተጫወተችውን ሚና አንስተዋል። ''እየተደማመጥንና እየተከባበርን የአገራችንን አንድነትና ጥቅም በማስቀደም ከሰራን ስራችን በራሱ ይሸልመናል'' ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሽልማቱ ሊኮራና ሊደሰት ይገባል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም