የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ...በኢሉ ገላን ወረዳ ከስደት ተመላሾች - ኢዜአ አማርኛ
የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ...በኢሉ ገላን ወረዳ ከስደት ተመላሾች
አምቦ ሰኔ 9/2010 መንግስት እያመቻቸ ባለው የስራ እድል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንዳልቻሉ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢሉ ገላን ወረዳ ከስደት ተመላሽ ወገኖች ገለጹ። የዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ከግማሽ ለሚበልጡት ከስድት ተመላሾች የስራ እድል ማመቻቸቱ ገልጿል፡፡ በወረዳው የኢጃጂ ከተማ ነዋሪዋ ከስደት ተመላሽ ወይዘሮ አበበች አበበ በሰጠችው አስተያየት ከአረብ ሀገር እንደተመለሰች የራሷን ስራ መስራት ብትፈልግም የመነሻ ካፒታል ችግር ገጥሟታል። ወደ ወረዳው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት በመሄድ ተደራጅታ ለመስራት የምትችልበት ሁኔታ እንዲመቻችላት በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ከጽህፈት ቤቱ በቂ ምላሽ እንዳላገኘች ገልጻለች። ሌላዋ ከስደት ተመላሽ ወይዘሪት ቆንጂት መስቀላ በበኩሏ የግለሰብ ቤት በመከራየት የጀበና ቡና በማፍላት እየሰራች ቢሆንም አሁንም የገንዘብና የመስሪያ ቦታ ችግር እንዳጋጠማት ተናግራለች። "መንግስት በማህበር አደራጅቶ ሁኔታዎችን ቢያመቻችልኝ በሀገሬ ሰርቼ የመለወጥ ሰፊ አላማ አለኝ " ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ ከስደት ከተለመሰች አንድ ዓመት እንደሆናትና እስከ አሁን ያለ ስራ እንደተቀመጠች የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ነኢማ ከድር ናት። ከአረብ ሀገር ይዛ የመጣችው ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ በግሏ ለመስራት በቂ አቅም እንደሌላት ገልጻ ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በመሆን የብድር አገልግሎት ብታገኝ የተሻለ የመስራት ፍላጎት እንዳላት ተናግራለች። በወረዳው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት የስራ ዕድል ፈጠራ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበበ ዋቅጋሪ በበኩላቸው ከተላኩላቸው ሶስት ማህበራት ውስጥ አንዱ የመስሪያ ቦታ እና የብድር አገልግሎት ማግኘቱን ገልጸዋል። ለተቀሩት ማህበራት የብድር እና የመስሪያ ቦታ እንዲመቻችላቸው እየተሰራ በመሆኑም በቅርቡ መፍትሄ ያገኛሉ ብለዋል ። የምእራብ ሸዋ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት የሰው ሃብት ልማት አስተዳደርና የስራ ዝግጁነት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጋዲሣ አበራ በበኩላቸው ወደ ዞኑ ከስደት ከተመለሱት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የስራ እድል ተመቻችቶላቸዋል። እስከ አሁን ድረስም በዞኑ ከስደት ከተመለሱት 250 ሰዎች መካከል ለ141ዱ የስራ እድል እንደተፈጠረ ገልፀው ቀሪዎቹም በቅርቡ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን አስረድተዋል። ከዞኑ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በዘንድሮው ዓመት ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል ከ85 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡