ቀጥታ፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጋምቤላና ትግራይ ክልሎች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጋምቤላ/መቀሌ መሰከረም 30/2012 ፡- የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጋምቤላ እና ትግራይ ክልሎች በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር የማመቻቸት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የየክልሉ ምክር ቤቶች አስታወቁ፡፡ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ላክደር ላክባክ እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልል ደረጃም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል። በተለይም በዓሉ በፓናል ውይይት፡በአካባቢ ጽዳትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በክልሉ ለማክበር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የፓናል ውይይቱ በሰንደቅ ዓላማ ጽንሰ ሀሳብና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ሀሳቦችን በማቅረብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ይካሄዳል፡፡ በአካባቢ ጽዳትና በሌሎችም ፕሮግራሞች በክልል ደረጃ ለማክበር እየተዘጋጁ መሆናቸውን አፈ ጉባኤ ላክደር ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በትግራይ ክልልም   ''ለህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችንና ለህገ_ መንግስታችን ልእልነት'' በሚል መሪ ሀሳብ  እንደሚከበር የክልሉ ምክር ቤት አስታወቋል። የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮንፍረንስ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታረቀ እንዳሉት ጥቅምት 3 ቀን ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል አከባበር የሚያስፈጽሙ ከክልል እስከ ወረዳ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። ኮሚቴዎቹ የሰንደቅ ዓላማ ምንነት የሚያስተምሩ የፌስቲቫልና ሌሎች ዝግጅቶችን የሚመሩ ናቸው። በዓሉን ምክንያት በማድረግ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የጽዳት ዘመቻ እንደሚካሄድም  አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል። በተለይም በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በዕለቱ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በመዘመር የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነስርዓት ይካሄዳል። በምሁራንና የህግ ባለሙያዎችም የተለያየ የፓናል ውይይት በየዞኑ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ   እንደሚካሄድ ተገልጿል። በዓሉ ሲከበር ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገር ሉአላዊነት መከበር መስዋእትነት የከፈሉ አባቶችም በመስታወስ ጭምር እንደሚከበር ተመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም