በትግራይ ወባና መሰል በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

58
መቀሌ ሰኔ 9/2010 ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ወባና መሰል በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት እያደረገ መሆኑ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቀ። ዝግጅቱ በተለይ ወባ፤ አተትና ውሃ ወለድ በሽታዎችን በወረርሽኝ እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰትም አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ነው። በቢሮው የበሽታዎች መከላከያ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ  ገብረሃዋሪያ እንዳሉተ እያንዳንዳቸው ስምንት አባላትን ያቀፉ የህክምና ኮሚቴዎች በየወረዳው ተቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ናቸው። እንዲሁም "ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ከእንሰሳት ሃኪሞች የተውጣጡ አባላት በህክምና ኮሚቴው እንዲሳተፉ ተደርጓል" ብለዋል። ወባ ለመከላከል ብሎም ለማስወገድ ስትራተጂ ተነድፎ በክልሉ ወባማ በሆኑ 21 ወረዳዎች ውስጥ የኬሚካሎችና የመድኃኒቶች ስርጭት ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል። አስተባባሪው እንዳመለከቱት የዝናብ ስርጭት በሚበዛባቸው ወረዳዎች አተትና የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰት ቅኝት የሚያደርጉ ባለሙያዎች ተመድቧል፣ የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎችም በበቂ ሁኔታ ተመቻችቷል። የወባ በሽታ ተጠቂ በሆኑ ወረዳዎች ለሚኖር ህዝብ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ የአልጋ አጎበሮች በበጀት ዓመቱ መሰራጨቱንና በክልል ደረጃ የአጎበር ሽፋን 91 በመቶ በላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል። በቃፍታ ሑመራ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የበሽታዎች መከላከል አስተባባሪ አቶ ሙለይ እምባዬ በበኩላቸው፣ ህብረተሰቡ በራስ ተነሳሽነት አካባቢው በማፅዳት፣ ውሃ የሚያቆሩና ረግረጋማ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን የመከላከል ስራው እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የወባ በሽታ የመከላከል ስራችን ብለን ይዘኗል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የባዕኸር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መብራት ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡ ትንኝ እንደሚረባባቸው የሚታወቁ አካባቢዎችን የመጥረግና የማዳፈን ስራዎች በየሳምንቱ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል ወይዘሯዋ። በጣንቋ አበርገለ ወረዳ  የአግበ  ቀበሌ አርሶ  አደር አብርሃ ተስፋይ በበኩላቸው "አካባቢያችን ወራጅ ወንዝ የበዛበትና በወባ ተጠቂ በመሆኑ በልማት ቡዱኖች ተደራጅተን ከወዲሁ ውሃ ወለድና አተት በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል እየሰራን ነው" ብለዋል። የበሽታዎቹ መከሰት ምልክቶች ሲታዩም ህብረተሰቡ በፍጥነት ሪፖርት እንዲያደርግ በየትምህርት ቤቱና የእምነት ቦታዎች የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም