ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ግኝት መፈታት አለባቸው - ሱዳን - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ግኝት መፈታት አለባቸው - ሱዳን
አዲስ አበባ መስከረም ኢዜአ መስከረም 30 ቀን 2012 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ግኝት መፈታት እንዳለባቸው የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሱዳኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በዚሁ ወቅት የሁለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ለግብጽና ሱዳን አመቺ በሆነ መንገድ እንዲገነባ ሁሉም ተባብረው መስራት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋዎች ሃላፊ ቢልለኒ ስዩም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች የልማት ስራዎች ከራሷ አልፋ ጎረቤት አገሮችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በትብብር የመስራትና በጋራ የመልማት ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል። ግድቡ የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማያሳድር መልኩ እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው፤ በግንባታ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ግኝት መፈታት እንደሚችሉ መግባባታቸውንም ነው ሃላፊው ያመለከቱት። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሶስቱን አገሮች ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን አገራቱ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በአገሮቹ መካከል የሚነሱ ጉዳዮችም በቴክኒክ ድርድሩ ሂደት እንደሚፈቱ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውም ተጠቅሷል። ኢትዮጵያና ሱዳን በዚህ በኩል ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸውም በማብራሪያው ተመልክቷል። ሱዳን በሽግግር ላይ የምትገኝ አገር እንደመሆኗ በአለም አቀፍ ደረጃ የተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲነሳላት ኢትዮጵያ እንድታግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጠይቀዋል። የሱዳን መረጋጋትና መበልፀግ ለኢትዮጵያ አቅምና ጥቅም መሆን እንደሚችል በውይይቱ ላይ ተገልጿል። ሱዳን በሽግግር ላይ እንደመገኘትዋ እያደረገች ያለው ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ አገሪቷ የጀመረችው ለውጥ አካታች እንዲሆን ሴቶችን በፖለቲካው ውስጥ ማሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። ትናንት በተካሄደው የአንድነት ፓርክ ምርቃት ላይ የተገኙት የኢጋድ አገሮች መሪዎች ጎን ለጎን ባደረጉት ምክክር ቀጣዩ የኢጋድ ፕሬዚዳንት የኬንያው ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ እንዲሆኑ መወሰኑ ተጠቁሟል።