ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቬል ሽልማቱ ይገባቸዋል -- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቬል ሽልማቱ ይገባቸዋል -- ምሁራን

ሀዋሳ/ሚዛን/ አርባምንጭ/ ሶዶ ኢዜአ መስከረም 30 ቀን 2012 ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆን በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ስኬታማ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን በደቡብ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማስፈን የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ብርታት እንደሚሆናቸውም ምሁራኑ ተናግረዋል ። ሙሁራኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ የተፈጠረውን ልዩነት ወደ አንድነት በማምጣታቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል ። በፍቅርና በመደመር እሳቤ በምስራቅ አፍሪካ ለሁለት አስርት ዓመታት በፍጥጫ ውስጥ በነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉት አስተዋጽኦ ለተሸላሚነታቸው ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር መልሰው ደጀኔ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚከተሉት አዲስ እሳቤ ከሀገር ባለፈ ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ በሶማሊያ ፣በሱዳን ፣ደቡብ ሱዳን ፣ በኤርትራና ጅቡቲ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለጀመሩት ስራ ትልቅ አቅም ይሆናቸዋል። ኢትዮጵያዊነት እንዲለመልም ለማድረግ ባከናወኑት ተግባር ልዩነትን በማስወገድ ለለውጡ ትልቅ ድጋፍ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ እንደሆነ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማምጣት የጀመሩትን ስራ በርካታ ደጋፊዎችን እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችላቸው መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው በውጪ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ምህረትአብ አብርሀም በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል አሸናፊ መሆናቸው እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉርም ኩራት የሚሆን ነው። በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለውን ለውጥ ለማገዝ አዲሱን ትውልድን የሚያነቃቃና የሳቸውንም ሌጋሲ ቀጣይ እንዲሆን መሰረት የሚጥል ነው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራቸውን ተጽእኖ ከፍ ማድረግ የሚያስችልና ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ በርካታ ደጋፊዎችን የሚያስገኝላቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህ የመላው ኢትዮጵያውያን ሽልማት ነው ያሉት አቶ ምህረትአብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩዋቸውን ስራ ከግብ እንዲያደርሱ ከጎናቸው እንድቆም የበለጠ የሚያነሳሳኝ ነው ብለዋል። መላው ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፔዳጎጂ መምህር ዶክተር ቤታ ፃማቶ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም ኖቤል አሸናፊ መሆናቸው ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ያለ ሰላም የሰው ልጆች ህይወት ትርጉም እንደሌለው ጠቅሰው በአገሪቱ የተፈጠረውን ልዩነትን ወደ አንድነትና ህብረት ለማምጣት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር እያቀነቀኑ በሃገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ምስራቅ አፍሪካ የሰላም ቀጠና እንድትሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ ከመሆናቸውም በላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ መሪ ናቸው ብለዋል፡፡ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት መምህር ጌታሁን ተሾመ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ በዋናነትም በተለያዩ አለም አቀፍ አደራዳሪ አገራትና ድርጅቶች ሳይሳካ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀወን የኢትዮ ኤርትራ ግጭት በአጭር ጊዜ እንዲፈታ ማድረጋቸው ለሽልማቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሽልማቱ ለሃገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረው ላልተፈቱ ውስጣዊ ችግሮች አቅም እንደሚፈጥርና አሁን ያሉ ልዩነቶችን ለማስተካከል በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የመደመር እሳቤው እንዲተገበር እያደረጉ ያለው ጥረት ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርሲው የማህበረሰብ ጤና መምህር ለሚ አበበ በበኩላቸው ሁሉም ሰው ሃሳቡን በነፃነት እንዲያንሸራሽር በሃገሪቱ የሚዲያ ነጻነት እንዲኖር ማድረጋቸው ሽልማቱ እንዲገባቸው አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል ። ሽልማቱ ከለውጡ ማግስት ወዲሀ አስጊ የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ በአመዛኙ እንዲስተካከል ማድረጋቸው ሃገራዊ ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ አንድነት እንዲመጣ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ እንዲጎለብት የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ተሸላሚ መሆናቸው የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች የህዝብን ፍላጎት ተከትሎ መምራት እንዲችሉ ትምህርት የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ የታሪክና ቅርስ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሃበሻ ሽርኮ ናቸው፡፡ ሽልማቱ ከማህበራዊ ጠቀሜታው ባሻገር የአገራችንን ገፅታ በማጉላት ቀጥተኛ የሆነ ቱሪዝም የመሳብ አቅም በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍም የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ትክክለኛነትና ህዝባዊነቱን የሚያሳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡