የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብሔራዊ የቁጠባ ቀን ሊያከብር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብሔራዊ የቁጠባ ቀን ሊያከብር ነው
መስከረም 30/2012 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ወር የሚቆይ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ብሔራዊ የቁጠባ ቀን ሊያከብር ነው፡፡ ባንኩ ቀኑን የሚያከብረው ከጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ "ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ እንቆጥብ" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ ባንኩ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ቅርንጫፎች በትምህርት ቤቶች፣ በገበያ ማዕከላት፣ ህዝብ በሚበዛባቸውና በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በቁጠባ አስፈላጊነትና ፋይዳ ዙሪያ ውይይት በማድረግ ንቅናቄ ይፈጠራል ብሏል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች፣ በንግድ ማዕከላት፣ በወታደራዊ ካምፖችና መሰል ተቋማት ንቅናቄ በመፍጠር የቁጠባ ሂሳብ በመክፈት ቀኑን የሚያከብረው መሆኑን እንዲሁ ጠቁሟል፡፡ የዜጎችን የተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማረጋገጥ፣ አገር ዓቀፍ ቁጠባን ለማነቃቃት፣ የተረጋጋና የሚያድግ ኢኮኖሚ መገንባትን ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ባንኩ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው የቁጠባ ቀን አማካኝነት ወሩን የገንዘብ አያያዝ፣ አጠቃቀምንና የቁጠባ ልምድን ለማሻሻል እንደሚጠበቅበትም ገልጿል፡፡ ባንኩ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የኢንቨስትመንት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ አካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በዚህም ለአገሪቱ ልማትና ብልጽግና የቆመ መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ አገራዊ ተቋም መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።