ቀጥታ፡

ድሬ ከነማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለምንም ግብ ተለያዩ

ድሬ ዳዋ ሰኔ 9/2010 በ27ኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ኢትዮ ኤልክትሪክን በሜዳው ያስተናገደው ድሬ ከነማ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ ድሬ ከነማ መከላከልን መሰረት አድርጎ ወደ ሜዳ የገባውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለማሸነፍ አልፎ አልፎ  ያደረጋቸው ሙከራዎች ሳይሳኩለት ቀርተዋል፡፡ የድሬ ከነማ ዋና አሰልጣኝ ስምኦን አባይ ዛሬ ቡድናቸው ሙሉ ለሙሉ በተናጠልም ሆነ በጋራ ጥሩ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ "በቀጣይ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሁሉንም ጥረት ይደረጋል” ብለዋል፡፡ "ድሬ ከነማ በሜዳው እንደማይሸነፍ ስለምናውቅ ወደ መከላከሉ በማዘንበልና ውጤት ተጋርተን ለመውጣት ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልናል" ያሉት ደግሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ምክትል አሰልጣኝ አቶ ለግአለ ዘውዴ ናቸው፡፡ በውጤቱ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው   ዛሬ ቢሸነፉ ቀጣዩን ጨዋታዎች አስቸጋሪ ያደርግባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የድሬ ከነማ አምበልና ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ "ዛሬ የማይጣል ነጥብ ነው የጣልነው ፤ በቀጣይ በማንም ውጤት ላይ ሳንንጠለጠል ሶስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት እንሰራለን" ብሏል፡፡ ድሬ ከነማ በመጪው ሐሙስ ከመከላከያ ጋር ያለበት የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ካደረገ በኋላ 28ኛው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን በሚቀጥለው  ሰኞ ከቡና ጋር አዲስ አበባ ላይ ይጫወታል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ውጤታቸው ድሬ ከነማ በ30 ነጥብ 12ኛ ኤሌክትሪክ በ29 ነጥብ 13 ኛ ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም