ቀጥታ፡

ጀርመን በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረጉ ተግባራትን እንደምትደግፍ ገለጸች

መስከረም 30/2012  ጀርመን በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረጉ ተግባራትን እንደምትደግፍ አስታወቀች። በጀርመን ምግብና ግብርና ሚኒስትር ጁልያ ሎክነር የሚመራ ልዑክ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዛሬ ጎብኝቷል። በጀርመን የምግብና ግብርና ሚኒስቴር የሚደግፈው በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የግብርና ምርታማነት መርሃ ግብር እ.አ.አ ከ2012 እስከ 2019 ሲተገበር ቆይቷል። ከ2012 እስከ 2015 በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ከቆየ በኋላ ውጤታማነቱ ሲረጋገጥ ወደ ትግበራ ተገብቷል። መርሃ ግብሩ በግብርና ምርምር የሚወጡ የተለያዩ የዘር አይነቶች ከምርት ጀምሮ አርሶ አደሩ እጅ እስኪደርስ ድረስ መደገፍ፣ በፖሊሲ ጉዳዮች የማመከር አገልግሎት መስጠት፣ አርሶ አደሮች አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ ማሰልጠንን ያካተተ ነው። ከዚህ ባለፈም በግብርና ሜካናይዜሽን ስልጠና የሚሰጠውና በኦሮሚያ አርሲ የተቋቋመው የቁሉምሳ ስልጠና ማዕከልም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። ሚኒስትሯ ጁልያ ሎክነር በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ ጀርመን ከአፍሪካ ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ትብብር አላት። ''ኢትዮጵያ ጠቃሚ አጋር ናት'' ያሉት ሚኒስትሯ አገሪቷ ያላትን ኃብት የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት መደገፍ ተገቢ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በኢትዮጵያ ያሉ አርሶ አደሮች ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማገዝ ከኛ የሚጠበቅ ነው ሲሉም ሚኒስትር ጁልያ የገለጹት። ለዚህም ለግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት በገንዘብ፣ በባለሙያና አስፈላጊው ቁሳቁስ የምንሰጣቸው ድጋፍ ተጠናቀሽ ናቸው በማለት አመልክተዋል። የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሙሳ ጃርሶ በበኩላቸው ማዕከሉ ከበርካታ አገሮችና ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስታውሰው ጀርመንም አንዷ መሆኗን ተናግረዋል። እንደ አቶ ሙሳ ገለጻ፤ በተለይ ለልምድ ልውውጥ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጀርመን ድረስ በመሄድ ልምድ እየቀሰሙ ነው። ይህም እንዲቀጥል ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም