የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

77
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 30/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማውን ደስታ በመግለጽ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ''የእንኳን ደስ ያላችሁ'' መልዕክት አስተላለፈ። በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያትም በሽልማቱ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ''የእንኳን ደስ ያላችሁ'' መልዕክት አስተላልፏል። በፅህፈት ቤቱ የፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋዎች ሃላፊ ቢልለኒ ስዩም በሰጡት መግለጫ ሽልማቱ ለተደረጉ ጥረቶች እውቅና የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያላትን የጎላ ሚና የሚያመላክት ሲሆን በቀጠናው አገሮች ሰላም ለማስፈን የተደረገውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑንም ገልፀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል አሸናፊነት ዓለም ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያደርግ አጋጣሚውን የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል። በመሆኑም በተገኘው ሽልማት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያሉትን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ሽልማቱ ይገባቸዋል የሚሉ ድምጾች አሸናፊነታቸውን ቀድመው እንዳወጁላቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፍረው ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል። በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ እድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል። የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው። በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል። በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለወጥ መስተካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ። በአጠቃላይ 301 እጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም