ያለፉት 130 ዓመታት ታሪክ ያለው የአንድነት ፓርክ ታሪክ ለአፍሪካዊያን ጭምር ነው...አቶ ንጉሱ ጥላሁን

መስከረም 29/2012 ያለፉት 130 ዓመታት ያለው አንድነት ፓርክ  የአፍሪካዊያን ታሪክ ጭምር ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ። የታላቁ ቤተ መንግስት ታድሶ 'የአንድነት ፓርክ' በሚል ስያሜ ለቱሪስት መዳረሻ ሊውል የተለያዩ ምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል። ''ባለፉት 130 ዓመታት ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ነጻ መሆን ከጎናቸው በመቆም ለተገፉት ደራሽ ነበረች ናት'' ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ''ይህ ታሪክ የተቦካበትና የተጋጋረበት ስፍራ ደግሞ ዛሬ የአንድነት ፓርክ በሚል በተመረቀው በታላቁ ቤተ መንግስት ነው'' ብለዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ባለፉት 130 ዓመታት በአፍሪካ ያከናወነችው ታሪክ መነሻው ይህ ቤተ መንግስት በመሆኑ፤ የስፍራው ታሪክ የአፍሪካዊያን ጭምር መሆኑን ተናግረዋል። ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ባስቆጠረው በዚህ ታሪክ ፊውዳል፣ የሶሻሊስትና የፌዴራል ስርዓት መንግስታት መስተናገዳቸውን አንስተው፤ ፓርኩ በሶስቱ ስርዓቶችንና በየስርዓቱ የነበሩ መሪዎችን ባህሪ፣ ድክመትና ጥንካሬ ለመዘከር እንደሚጠቅም ተናግረዋል። የአንድነት ፓርክ የተባለውም ባለፉት ዓመታት በነበሩ ታሪኮች የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል፣ የተፈጸሙ ስህተቶችን በማረም የነገ ጠንካራና አንድነቷ የተጠበቀ አገር ለመገንባት ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አንስተዋል። ከትናንት ተምረን ዛሬ ላይ በአንድነት ከተጋን አንድነቷ የተጠበቀ አገር መፍጠር አለብን ሲሉም ገልጸዋል። መለያየትን የሚያስቡ ደካሞች ናቸው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ የአንድነት ፓርክ አንድነትን በሚያስቡ ጠንካራ አስተሳስቦችና ኢትዮጵያዉያን የሚስማሙበት ታሪክ ስላለው በአንድነት ተምሳሌትነት መመስረቱን ነው የተናገሩት። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተጀመረው ቅርሶችን አድሶ ለቱሪዝም መዳረሻነት የማዋል ተግባርም ወደፊት በክፍላተ አገሮች በሚገኙ መካነ ቅርሶች እንደሚቀጥል ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም