ለተማሪዎች የሚሰጠው የማማከር አገልግሎት ወቅቱን የጠበቀ አይደለም - --የጋይዳንስና ካውንስሊንግ መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ለተማሪዎች የሚሰጠው የማማከር አገልግሎት ወቅቱን የጠበቀ አይደለም - --የጋይዳንስና ካውንስሊንግ መምህራን
መስከረም 29/2012 በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች እየተሰጠ ያለው የማማከር አገልግሎት ችግሮችን በራሳቸው መቋቋም በሚችሉበት ጊዜ መሆኑ ሂደቱን ያልተከተለ እንደሚያደርገው ተገለጸ። በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ማማከር አገልግሎት ተማሪዎች ራዕያቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት የትምህርት ጉዞ የሚገጥሟቸውን መሠናክሎች በራሳቸው የመፍታት አቅምን የመገንባት ስራ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ መምህራን አገልግሎቱ ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲገቡ ከሚሰጥ ይልቅ የወደፊት ሥነ-ባህሪያቸው መሠረት በሆኑት በቅድመ-መደበኛና በመደበኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአስገዳጅነት ሊተገበር ነው የሚገባው ይላሉ። መምህራኑ የእስካሁን የአገልግሎት አሰጣጡን ተግዳሮቶች የገለጹት ከፊደል ጋር ባለመጀመራቸውና ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ተከትሎ ባለመታነፃቸው ለውጥ አያመጣም፤ አላመጣምም በማለት ነው። በትግበራ ላይ ያለው የማማከር አገልግሎት በቅድሚያ ለቅድመ-መደበኛና ለመደበኛ መጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ተግባራዊ ቢሆን፤ ወደ 2ኛ ደረጃ ሲገቡ በአማራጭነት ቢያዝ ውጤታማ ይሆናል ነው ያሉት። የሀዋሳ ታቦር መሠናዶ ትምህርት ቤት የጋይዳንስና ካውንስሊንግ መምህሩ ዮሴፍ ፈለቀ "የምክር አገልግሎቱን ከታችኛው የክፍል ደረጃ ባለመጀመራችን ካገኘነው ጥቅም ያጣነው ይበልጣል" ብለዋል። መምህር ዮሴፍ ተማሪዎቹ እስከ መጀመሪያ ደረጃ ማጠናቀቂያ ችግሮችን እንዴት በራሳቸው መፍታት እንዳለባቸው ልምድና ክህሎት ሳይለማመዱ ማደጋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በዚህ ሳቢያ 'ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብንደክምላቸው፤ ኮሌጅም ሆነ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የመፍታት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል' ሲሉም አክለዋል። ለአገልግሎቱ መዳበር አስተዋጽኦ ማድረግ ያለባቸው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቢሮዎች፣ ትምህርት መምሪያና ጽህፈት ቤቶች ለዚህ አገልግሎት አደረጃጀት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል። "ለተማሪዎቻችን የምንሰጠውን የጋይዳንስና ካውንስሊንግ አገልግሎት ማቆም በሚቻልበት ወቅት እየጀመርን ነው" ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ሚሊኒየም መሠናዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ጌትነት ተሾመ ናቸው። አገልግሎቱ የተማሪዎችን ባህሪ ማነጽ፣ ከሱስ የፀዱ ማድረግ፣ ማህበረሰቡን የሚያከብሩ፣ የሰዎችን ችግር በቀላሉ የሚረዱና የሚጋሩ አይበገሬና ፅናትን የተጎናፀፉ ማድረግ መሆኑንገልጸዋል። "አሁን በተማሪዎች የሚንፀባረቀው የሕይወት ክህሎት ችግር የምክር አገልግሎቱን ከመሠረቱ ባለመጠቀማቸው የመጣ ነው" ያሉት መምህሩ የተግባቦት፣ መልካም ግንኙነት፣ የብቃት መዋዠቅና በማንነት ያለመተማመን ችግሮችንም ጭምር ጠቅሰዋል። መምህራኑ አሁን በተማሪዎቹ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ባለሙያዎች፣ የትምህርት ተቋማትና መንግስት ጉዳዩን ቢመረምሩት ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። አገልግሎቱን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመጀመር ሊያጋጥም የሚችለውን የመምህራን እጥረት አጫጭር የካውንስሊንግና ጋይዳንስ ስልጠናዎችን በመስጠት የሚጀመርበትን አማራጭም ጠቁመዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉም መምህራኑ የሰጡት ምክረ-ሀሳብና አስተያየት ተገቢ መሆኑን ገልጸው አዲሱ ፍኖተ-ካርታ በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ትግበራ ሲመጣ ይኸው አገልግሎት ይኖራል ነው ያሉት። በሁለተኛ ደረጃ እንደተቀመጠው ለአንደኛ ደረጃ ካውንስለር ተብሎ አይቀመጥ እንጂ አገልግሎቱን አካታች በሆነ መንገድ የሚሰጡ ርዕሰ-መምህራን፣ መምህራንና እንደ ስነ-ጾታ ያሉ ክበባት መኖራቸውን ገልፀዋል። ሚኒስቴሩ ይህንንም ለማገዝ ከራሱ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ባሉ መዋቅሮቹ ከስነ-ምግባር ቀረጻ ጋር አያይዞ በመከታተልና ከአጋር አካላት በመተባበር አጫጭር ስልጠናዎች እየሰጠም ነው ብለዋል። እንደ ሚኒስቴር ዴኤታዋ ገለጻ፤ በፍኖተ ካርታው ምክረ-ሀሳብ መሰረት የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ቅድሚያ በመለወጥ ወደፊት የግል ትምህርት ቤቶችም እንዲከተሉ ይደረጋል። የማማከር አገልግሎቱ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው በተገቢው የትምህርት ደረጃና ዕድሜ አይደለም ቢባልም በግል ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ አይደለም።