በታላቁ ቤተ መንግስት የተገነባው የአንድነት ፓርክ ለህዝብ ክፍት ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ቤተ መንግስት የተገነባው የአንድነት ፓርክ ለህዝብ ክፍት ሆነ
መስከረም 29/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህምድ ዛሬ በይፋ ፓርኩን መርቀው የከፈቱ ሲሆን ፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩቬሪ ሙሶቬኒ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር፣ ጨምሮ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ባለስልጣናት በስነ-ስርዓቱ ላይ ታድመዋል። ፓርኩ የአረንጓዴ ስፍራ፣ የጥቁር አንበሳ ዋሻ፣ የአገር በቀል እጽዋቶች ስፍራ፣ የዘጠኙም ክልሎች እልፍኞች ታሪካዊ ህንጻዎችና ሙዚየም እንዲሁም የመካነ እንስሳት ያካተተ ስድስት የመስህብ ስፍራዎች አሉት። የአረንጓዴ ስፍራው ጎብኝዎች የእግር ጉዞ የሚያደረጉባቸው መንገዶች የህጻናት መጫዎቻዎችና እረፍት መውሰጃ ቦታዎችን አካቶ ይዟል። እንደ ጤና አዳም፣ ዳማ ከሴና ኮሰረት የመሳሳሉ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ የሚጠቀሟቸው እጽዋቶችም የአገር በቀል የእጽዋት ስፍራው አካል ናቸው። የጥቁር አንበሳ ዋሻው ደግሞ አንድ እንስት እና አንድ ተባእት አንበሳዎች እንዲኖሩበት ተደርጎ በድንጋይ የተገነባ ነው። ዘጠኝ የሚደርሱት የክልል እልፍኞች በወከሉት ክልል ውስጥ ያሉ አንኳር የባህልና የታሪክ መስህቦችን በሚገልጽ መልኩ በማራኪ የአርክቴክት ጥበብ ተሰድረው ተቀምጠዋል። ከ130 ዓመት የሚጠጋ እድሜ ባስቆጠረው በዚህ ታሪካዊ ቤተ መንግስት በሚገኙት ጥንታዊ ህንጻዎች ውስጥ እድሜ ጠገብ የንጉሳውያንን ቁሳቁሶች ከያሉበት ቦታ ተሰብስበው ለጎብኝዎች ክፍት ሆነዋል። ከአጼ ምኒሊክ እስከ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ድረስ ኢትዮጵያን ያስተዳዳሩ ግለሰቦች የሚገለጹባቸው አበይት ኩነቶችም ሙዚየም እንዲይዛቸው ተደርጎ ለጉብኝት ክፍት ተደርገዋል። ፓርኩ ካሉት መስህቦች መካካል አምስቱ ዛሬ ለህዝብ ክፍት የሆኑ ሲሆን፤ ከ46 በላይ የእንስሳት ዝርያን እንዲይዝ ተደርጎ እየተገነባ ያለው መካነ እንስሳት ደግሞ በቀጣይ ህዳር ወር ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል። ፓርኩን በማደራጀት ስራ ላይ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን ጨምሮ ስድስት የሚደርሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ባህል ምሁራን መሳተፋቸውን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ የስራ ባልደረባ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት 'ቤተ መንግስቱ ለህዝብ ክፍት ይሁን' የሚለው ሃሳብ ትልቁ የፖለቲካ ወሳኔ መሆኑን ይናገራሉ። ውሳኔው ህዝብን ከታሪክ የሚያገናኝ መሆኑን በመጠቆም። ''የፓርኩ መከፈት ሶስት ትውልድን በአንድ ስፍራ ያገናኛል'' ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ይህም የፓርኩ ሌላኛው ልዩ ገጽታ መሆኑን ገልጸዋል። ስፍራውን የሚጎበኙ የቀደመው ትውልድ ሰዎች በግለሰቦች እጅ የሚገኙ ጥንታዊ ቁሳቁሶችን በማምጣትም ሆነ በመጠቆም ለፓርኩ መሟላት የሚያግዙበት እድል የሰፋ መሆኑንም አውስተዋል። ፓርኩን መጎብኘት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ዜጎች መደበኛ 200 እንዲሁም ልዩ (ቪአይፒ) አንድ ሺህ ብር፤ ለውጭ አገር ዜጎች ደግሞ መደበኛ 20 እንዲሁም ልዩ 50 ዶላር የመግቢያ ተመን ወጥቶለታል። ለጉብኝቱ ከጥሬ ገንዘብ ክፍያ ውጭ ያሉ አማራጮች የተዘጋጁ ሲሆን 6030 በመደወል ካርድ ማስቆረጥ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክሬዲት ካርድ ማስቀነስ እንዲሁም በፓርኩ በር ላይ በተዘጋጀ ፖስ ማሽን መክፈል እንደሚቻል ተገልጿል። ፓርኩ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ መጠናቀቁንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።