ቀጥታ፡

12ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በመጪው ሰኞ ይከበራል

መስከረም 29/2012  12ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በመጪው ሰኞ እንደሚከበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ። ምክር ቤቱ የበዓሉን አከባበር አስመልከቶ በሰጠው መግለጫ በተሻሻለው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር መደንገጉን አስታውሷል፡፡ በዓሉ “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበር መሆኑም ተገልጿል። በህዝቦች አንድነት ላይ የጋራ መግባባት በሚፈጥር መልኩም ውይይት በማድረግ በዓሉን ማክበር እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል። በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በአዋጆች ዕውቅና ያገኘውን ሰንደቅ ዓላማን ማክበርና በጋራ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ተገቢ መሆኑንም ነው የተገለጸው። የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰንደቅ ዓላማን የነፃነታቸውና የሉዓላዊነታቸው ምልክት አድርገው የመረዳት የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳላቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል ፡፡ ባለፉት አመታት ውስጥ የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት መገለጫና ለህዝቦች ዲሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ሥራ መሰራቱም ተመልክቷል፡፡ ሰንደቅ ዓላማው የሉዓላዊነት መገለጫና የአንድነት ምልክት መሆኑ ላይ የጎላ ልዩነት ባይኖርም በዓርማው ላይ ግን በሚፈለገው ደረጃ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንዳልተቻለ ይታወቃል ተብሏል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ላይም በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሕዝብ ጋር በሚኖር ውይይት የሚነሱት ጥያቄዎች እየተመለሱና መግባባት እየተፈጠረባቸው ይሄዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል፡፡ በተያዘው ዓመት የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ማክበር የሚነሱትን የተለያዩ ጥያቄዎች ለህዝብ በማቅረብ በለውጡ ሂደት ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛልም ተብሏል፡፡ በዓሉ የፖለቲካ ፖርቲዎችና ደጋፊዎቻቸውም የጋራ በሚያደርጉ ሀገራዊ እሴቶች ላይ እንዲወያዩ እድል እንደሚሰጥም ተጠቅሷል፡፡ ህዝቡ በሰንደቅ ዓላማ የምትወከል የጋራና የሚወዳት ሀገር እንዳለው በማረጋገጥ ለመወያየትና የሃሳብ ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተናገድ እንዲቻልም ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡ ዜጎች በልዩነት በሚያነሷቸው ጉዳዩች ላይ የተደራጀ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በህግ የጸደቀውን የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ በማክበር ላይ አቋም እንዲይዝ ለማድረግም እንደሚያስችልም ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም