ቀጥታ፡

ወዮ ወዮ ...... የአገር በቀል ዕውቀት ነገር....

አየለ ያረጋል- ኢዜአ የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያ ከሻሸመኔ- አርባምንጭ መንገድ 65 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።54 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ይህ መጠለያ ታዲያ ሰፊ ችግር ነበረበት፤ ይቃጠላል፤ ደኑ ይጨፈጨፋል። ብርቅዬ እንስሳቱም የመጥፋት አደጋ ተጋረጠባቸው። መንግስትም እንስሳቱን ከችግር ለመታደግ ወይንም መጠለያውን ከጥፋት ለመጠበቅ በተደጋጋሚ ጣረ፤ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ጀመረ። ግን ከጥፋት መታደግ አልቻለም። በአንድ ዕለት የጎሳ መሪዎች ለጥቂት ሰዓታት ተሰባሰቡ፤ ብርቅዬ ቆርኬዋን ለጎሳ አባል አድርገው ሾሟት። በአካባቢው ባህል ወይም የጎሳ አስተዳድር ህግ መሰረት የጎሳውን አባልና ንብረት ማጥፋት ውግዝ ነው። እናም ብርቅዬዋ ቆርኬ የጎሳውን አባልነት ከተቀላቀለችበው ዕለት ጀምሮ ሰላም ወረደላት። እርሷም ሆነ መጠለያዋ ከጥፋት ተከበረላት። ለዓመታት ከተጋረጠባት የአኗኗር ሰቆቃ ተርፋ ዝርያዋን እየተካች መኖሯን ቀጠለች። ይህን መረጃ ሹክ ያለኝ ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ነው። በዛሬ ዕለት በአገር በቀል የአስተዳድር፣ ህግና ፍትሕ ስርዓቶች ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ ምርቃ ነበር፤ በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ። በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቶች ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታህ አብደላሂ የተዘጋጀው መጽሐፉ  'የደራሸ ወረዳ ሕዝቦች  የባሕል ሕግ ስርዓት' በሚል ርዕስ ነው የታተመው። በዚህ መድረክ የአገር በቀል ወይም የባህል የአስተዳድር፣ የሕግና ፍትሕ ስርዓቶች ለአገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት ያላቸው ሚና እንዲሁም ለአገራዊ የአስተዳድር፣ የሕግና ፍትሕ ስርዓቶች የሚያበርክቱት አስተዋጽ በሚል ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎ ነበር። በርካታ የሕግ ምሁራንም መድረኩን ታድመዋል። ከተሳታፊዎች መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በኢትዮጵያ የአብዛኞቹ ብሔረሰቦች የባሕል እሴት የተገነባባት ቋንቋ ቢለያይም የእሴቱ ታህታይ መዋቅር ግን ተመሳስሎሽ እንደለው ይገልጻል። ነገር ግን በየማህበረሰቡ ያለውን የአገር በቀል ወይም ባሕላዊ ስርዓቶች ተመሳስሎሽ አጥንቶ አንድ ወጥ አገራዊ የሕግ ስርዓት መገንባት ለምን አልተቻለም? በማለት ይጠይቃል። "አባቶች ለዘመናት ሲገለገሉባቸውና ማህበረሰባቸውን ማህበራዊ ኑባሬ ሲዳኙባቸው የቆዩባቸውን እነዚህ ስርዓቶች የመሰረቷቸው በዩኔስኮ ዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብላቸው ፈልገው አይደለም፤ ለሚያጋጥማቸው ውስጣዊ ችግሮቻችው ውስጣዊ መፍትሔ ለማበጀት እንጂ" በማለት ያብራራል። ይሁንና ኢትዮጵያ 'ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ' ከሚለው የመንግስት ስርዓት ስያሜ ጀምሮ በቋንቋ ባህል፣ በአስተዳር፣ ሕግና ፍትህ አገር በቀል ዕውቀቷን አስተሳስራ አልተጓዘችም ይላል። አገር በቀል ባሕላዊ ሕግጋት ለሰላም፣ ለአገር አንድነትና ልማት ሚናቸው ከፍተኛ ነው የሚለው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ባሕላዊ ስርዓቶችን በቅርስነት ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን በስርዓቶቹ መገልገል ችግሮችን መፍታት ይገባል ይላል። በርግጥም አገር በቀል ስርዓቶች ምን ያህል ለማህበረሰቡ ውስጣዊ ችግሮች መድሃኒት እንደሆኑ ከላይ የተጠቀሰው የቆርኬዎች ጉዳይም  ጥሩ ማሳያ ይመስላል። አንጋፋው ጸሐፈ ተውኔት አያልነህ ሙላቱም ይህን ሃሳብ ይጋራል። የአገር በቀል ዕውቀት አጠቃቅም ችግር ከትምህርት መሰረቱ የተበላሸ እንደሆነ ይነገራል። "የትምህርት ስርዓቱ 'አቡጊዳ' በ'ኤ ቢ ሲ ዲ'፤ የ'ቆሎ ተማሪ' በ'ዳቦ ተማሪ' ሲተካ አገራዊና የውጪውን አስተሳስሮ የተሄደ አልነበረም የሚለው የተውኔት ባለሙያው፤ እንደ ቻይናና ጃፓን አገር በቀል ዕውቀቶችንም ከዘመናዊ ስርዓቶች ጋር አጣጥሞ መሄድ ቢቻል ኖሮ ለዚህ 'ወዮ ወዮ' አይደረስም ነበር" ይላል። “የሀገር በቀል ወይም የባህል የአስተዳደር፣ የህግ እና የፍትህ ስርዓቶች ለሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ የውይይት ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርትን ሲጀምሩ ሰው ተምሮ አገሩን እንዲያበለጽግ እንጂ የራሱን ባህል እንዲያፍር አልነበረም ይላሉ። ኢትዮጵያ ከራስ ዳሽን በርዷማ ስፍራ እስከ ዳሉል የእሳት እቶን ብዝሀ ሕይወት ባለጸጋ ናት የሚሉት ፕሮፈሰሩ፤ በዚህ ብዝሀ ሕይወት ውስጥ ብዝሀ ባህል ያላቸው ሽዝቦች ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል። የኛ ሕዝብ የባህል እሴት 'ማህበራዊ' መሆኑን ገልጸው፤ ስርዓቶቹ 'ግላዊ የአኗኗር ዘይቤ' ከሚከተሉ ምዕራባዊን አገራት የተኮረጁ የአስተዳድር፣ የህግና ፍትህ ስርዓቶች ጋር ተጣጥመው አለመተግበራቸውን ይናገራሉ።"የኢትዮጵያ ህዝቦች በየዘመናቱ በርሃብ፣ በጠላት ወረራ፣ በንግድ፣ በዕውቀት ፍለጋና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች ተዛንቀዋል" ይላሉ። በዚህ መዛነቅ ሂደት ሁሉም ማህበረሰብ የሚያጋሯቸው አገር በቀል ባህል፣እሴት፣ ዕውቀቶች ባለቤት እንደሆነ ገልጸው፤ እነዚህን ባህላዊ ስርዓቶች ወደ አንድ ወጥ አገራዊ ስርዓት ለማምጣት የሚቻለው በቅድሚያ የየብሔረሰቡ ዕውቀቶች ሲሰባሰቡ እንደሆነ ያምናሉ። በዚህም የኢትዮጵያ ፍትሕ ስርዓቶች ማዕከል የሚያደርጋቸው ጥናቶችና ህትመት ውጤቶች መልካም ጅምር መሆናቸውን ያብራራሉ። የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቢሰጥ በየነ ግለሰብ ከራሱ፣ ከመሰሉና ከአካባቢው ጋር በሚፈጥረው ግንኙነት የባህል አስተዳደር ህጎች እንደሚዘረጋ ይናገራሉ። በዚህ ሂደት በኢትዮጵያም በርካታ አገር በቀል እውቀቶች አንዳሉ ገልጸው፤ እነዚህ ባህላዊ ስርዓቶች በአገራዊ ህጎች ቢካተቱ ማህበረሰቡ የቆዩ በመሆናቸው በማህበረሰቡ ፍትህና ዳኝነት ዘርፍ በቀላሉ ቅቡልነት እንዲያገኙ ያችላሉ ይላሉ። ከዚህ በፊት የተቀረጹ ህጎች በማህበረሱ ባህልን መሰረት ያላደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ አገራዊ የአስተዳድር፣ የህግና ፍትህ ስርዓቶች ቢካተቱ ህጎችን በቀላሉ በማህበረሰቡ ለማስረጽም ያገለገላሉ ባይ ናቸው። በዚህ ሂደትም ማህበራዊ ዕድገት ማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል። የሕግ ጠበቃው አቶ አበበ አስራደው በበኩላቸው አገር በቀል ሁለገብ ዕውቀቶች በተግባር ለመለወጥ ጥናት ማድረግ የስፈልጋል ይላሉ። አገሪቷ ለሚያጋጥማት ውስጣዊ ችግሮች መፍትሔ አገር በቀል ወይም የባህል እሴቶችን መጠቀም ሲቻል እንደሆነም ገልጸዋል። በተለይም በአስተዳድር፣ በህግና ፍትሕ ስርዓቶች የፖለሲ ጥናት ተደርጎ በአገራዊ ህጎች መካተት እንዳለባቸው ነው የተገጸው። "በአፋር ባህል መሰረት ሰው የገደለ በግመል ካሳ ከፍሎ ይታረቃል፤አዲስ አበባ ሰው የገደለ 20 ዓመታት ይታሰራል፤ ሁለቱም የሚዳኙት ግን በአንድ አገራዊ የወንጀል ህግ ነው" የሚሉት አቶ አበበ፤ ባህላዊና ዘመናዊ የፍትህና ዳኝነት ስርዓት በደንብ ሊጤን የሚገባው እንደሆነ አብራርተዋል። በአገራዊ 'በለጋሾች በጀት የሚሰራ ጥናት በራሳቸው ፍላጎት ብቻ የሚመራ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ በጀት በጅተው በአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ መስራት እንደለባቸው ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል። አገር በቀል የአስተዳድር፣ የሕግና ፍትሕ ስርዓቶች በተግባር ላይ ካሉት አገራዊ የሕግ ስርዓቶች ጋር አዋህዶ በፖሊሲ ደረጃ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ነው በብዙኃኑ ተሳታፊ በኩል የተስተጋባው። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ የመንግስት ስርዓት ባለቤት መሆኗን የጠቀሱት በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ፤ እነዚህን አገር በቀል ዕውቀቶችን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህም የግልና መንግስታዊ ተቋማት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው መንግስት በዘርፉ ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፉን አንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም