በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጀመሪያው ብሔራዊ ፓርክ ለአገልግሎት እየተመቻቸ ነው

84
አሶሳ ኢዜአ መስከረም 29/2012 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጀመሪያው ብሔራዊ ፓርክ ለአገልግሎት እየተመቻቸ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሰታወቀ። በቢሮው የፓርኮች እና ዱር እንስሳት መጠለያ ስፍራ ልማት ዳይሬክተር አቶ ባዬ ወዳይ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ መተከል ዞን ጉባ እና ዳንጉር ወረዳዎች "ቢጀሚዝ" በሚል የተሰየመው  ብሄራዊ ፓርኩን ለአገልግሎት ለማመቻቸት  ጥናት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ 181 ሺህ 628 ሄክታር በሚሸፍነው ይኸው ብሔራዊ ፓርክ አንበሳ፣ ነብር፣ ጉሬዛ፣ አጋዘን፣ ድኩላ፣ የተለያየ ተሳቢ እንስሳት እና አእዋፍ  ይገኙበታል። የቆላ ቀርከሃ፣ ግራር፣ ዋርካ እና ሌሎችም የፓርኩ ተጠቃሽ እፅዋቶች ሲሆኑ የፓርኩ መጠሪያ የሆነውን ቢጀሚዝ እና ሌሎችንም ወንዞች ያካትታል ብለዋል ዳይሬክተሩ ፡፡ ጥንታዊው የደጃዝማች መሃመድ ባንጃው ቤተ-መንግስት እና ደቀ-ማርማያም እና ደቀ-እስጢፋኖስ ገዳማትም በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 2 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት በዳጉር ወረዳ ቆታ ቀበሌ የተጀመረው የብሔራዊ ፓርኩ ጽህፈት ቤት ግንባታ መጠናቀቁን ዳይሬክተሩ  ጠቅሰዋል፡፡ 14 ስካውቶች ስራ መጀመራውን ያመለከቱት  አቶ ባዬ "የጽህፈት ቤቱ መዋቅር ተዘጋጅቶ ቅጥር እየተፈጸመ ሲሆን በ2013 ሙሉ በሙሉ የማስጎብኘት ሥራ ለማስጀመር ታቅዷል" ብለዋል፡፡ ፓርኩን ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ዓመታት የፈጀ ውይይት እና ጥናት መደረጉን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ የክልሉ ምክር ቤት ከአራት ዓመት በፊት ፓርኩን በአዋጅ ማጽደቁን አስረድተዋል፡፡ ህብረተሰቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ሌላ በካማሽ ዞን የያሶ ዲዴሳ፣ የማኦኮሞ እና የወምበራ ቡለን ዕጩ ብሐሄራዊ ፓርክ ለማድረግ በተያዘው  ዓመት ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ሰደድ እሳት፣ የመሬት ወረራ፣ ህገ-ወጥ ደን ጭፍጨፋ ዋነኞቹ የብሔራዊ እና ዕጩ ፓርኮቹ  ፈተናዎች ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት ቢሮው ያለበት የባለሙያ፣ በጀትና ተሸከርካሪ ችግር ስራውን ለማከናወን   የሚያደረገውን ጥረት ውስን አድርጎታል፡፡ የተፈጥሮ ሃብት ለትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር ለሃገር ኢኮኖሚ ለማዋል የተጀመረውን ጥረት ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም