በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን የውጭ አገራት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን የውጭ አገራት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ገለጹ
መስከረም 28/2012 በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለመሰማራት በዘርፉ ያሉ አድሎችና አማራጮች ላይ ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን የውጭ አገራት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ገለጹ። 10ኛው "አዲስ ቢውልድ" ዓለም አቀፍ የኮንስራክሽን፣ ብረታ ብረት፣ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና የመሰረተ ልማት አውደ ርዕይ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል። በአውደ ርዕዩ ላይ ከ70 በላይ የውጭ አገራት ኩባንያዎች እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን ኢዜአ በአውደ ርዕዩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙትን የውጭ ኩባንያዎች አነጋግሯል። የቱርክ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ህንድ፣ ኦማን፣ ታይላንድ፣ ኩዌት፣ ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ዩክሬንና ኳታር ኩባንያዎች በአውደ ርዕዩ ላይ ይሳተፋሉ። የኳታር የብረታ ብረት አምራች ኤስ ቢ ኤስ ስቲል ኩባንያ ኦፕሬሽን ማናጀር ዩሱፍ ኖፋል ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልጸው በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እያደገ መምጣቱንና የዚህንም መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን እድገት በአፍሪካ ካሉ አገራት በፍጥነት እያደገ እየመጣ እንደሆነም ግንዛቤ እንዳላቸውና በዚህም ምክንያት በአውደ ርዕዩ ለማሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡና በመዲናዋ ብዙ የኮንስትራክሽን ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ለመመልከት መቻላቸውን የገለጹት ማናጀሩ፤ ከአዲስ አበባ ውጭም የተለያዩ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን መስማታቸውንም አመልክተዋል። በአውደ ርዕዩ ላይ ኩባንያው የተሳተፈው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ባለው ፍላጎት እንደሆነና አውደ ርዕዩም ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ያሉትን አማራጮችና እድሎችን ለመመልከት የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነም ነው ሚስተር ዩሱፍ የገለጹት። በአፍሪካ ከዚህ በፊት በኬንያ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት ሚስተር ዩሱፍ ከአውደ ርዕዩ በኋላ በድጋሚ ጉብኝት በማድረግ ኩባንያቸው የስራ ግንኙነት ካደረጋቸው የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በመወያየት የትስስር ቢሮ ለመክፈት እቅድ እንዳለውም አክለዋል። ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገውና የኮንክሪት አምራች ኩባንያ የሆነው የኮሎምቢያ ማሽን ኢንጂነሪንግ የዓለም አቀፍ ሽያጭ ስራ አስኪያጅ ሚስ ሀሪሽ ራህማን በበኩላቸው ኩባንያቸው በአውደ ርዕዩ ላይ ሲሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ ይገልጻሉ። ኩባንያቸው ባለፈው ዓመት በአውደ ርዕዩ ተሳትፎው ከኢትዮጵያ የኮንሰትራክሽን ኩባንያዎች ጋር የስራ ግንኙነት መፍጠሩንና ከኩባንያዎቹ ጋር ውይይት በማድረግ በኢትዮጵያ ያለውን የዘርፉ እድገት ላይ ጥናት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዘርፉ ካሉ ችግሮች ዋነኛው እንደሆነና የአገሪቷ የኢኮኖሚ አቅም እያዳበረ ሲመጣ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በጥሩ እድገት ላይ እንደሚገኝና በዘንድሮው አውደ ርዕይም ባለፈው ዓመት የተጀመረውን ትስስር በማጎልበት ያሉትን አማራጮችና እድሎች ኩባንያው በጥልቀት ይዳስሳል ብለዋል። በቀጣይ ዓመታትም በዘርፉ ያለውን ሁኔታ በመመልከት ኩባንያው መዋዕል ነዋዩን ሊያፈስ እንደሚችል ጠቅሰዋል። የጀርመኑ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና የሞባይል አምራች ኩባንያ የሆነው ሽዊንግ ስቴተር የቢዝነስ ተቋም የሆነው ሜሞ ኢንዱስትሪያል ፕላኒንግ የሽያጭ ሃላፊ ሾክሪ ገማል ኩባንያቸው በአውደ ርዕዩ ላይ ሲሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት የመንገድ፣ የባቡር፣ ግድቦችና ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንና ይሄም በኮንስራክሽን ዘርፍ ለተሰማራ ኩባንያ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። ኩባንያቸው በአውደ ርዕዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፍ እንጂ ከዚህ በፊት የኩባንያው የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያ በመምጣት በዘርፉ ስላለው ሁኔታ ምልከታ ማድረጋቸውንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት የኮንስትራክሽን ስራዎች በፍጥነት እንዳይከናወኑ እንደሚያደርግና ችግሩን ለመፍታትም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል። የቱርክ የኤሌትሪክ ሃይልና የግንባታ ኩባንያ የሆነው ኢኮስ ግሩፕ የገበያና ቢዝነስ ልማት ስራ አስኪያጅ ሚስ አይሴል አባሊ ኩባንያቸው በአውደ ርዕዩ ላይ ሲሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነና በአውደ ርዕዩ አማካኝነት በኢትዮጵያ ያለውን የገበያ አማራጭ እንደሚዳስስ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኩባንያቸው በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፈው በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን የቢዝነስ አማራጭ ይበልጥ ለመረዳት እንደሆነም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ሰፊ የግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ኩባንያቸው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግንባታ ላይ በመሳተፍ ለግንባታዎቹ የሚያስፈልገውን የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል። በአውደ ርዕዩ ላይ ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በቀጣይ በጋራ መስራት የሚቻልባቸው ሁኔታዎችንም ኩባንያው እንደሚመለከት አክለዋል። 10ኛው "አዲስ ቢውልድ" ዓለም አቀፍ የኮንስራክሽን፣ ብረታ ብረት፣ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና የመሰረተ ልማት አውደ ርዕይ እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ይቆያል።