በኢትዮጵያ ለአእምሮ ህመም ህክምና አገልግሎት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለአእምሮ ህመም ህክምና አገልግሎት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
መስከረም 28/2012 በኢትዮጵያ ለአእምሮ ህመም ህክምና አገልግሎት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎች ተናገሩ። የአማኑኤል ስፔሻላይዘድ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመሆን የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን ምክንያት በማድረግ ‘ትኩረት እራስን ማጥፋት ለመከላከል’ የሚል መሪ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት የአእምሮ ህመም በኢትዮጵያ ከሌሎች የጤና ችግሮች ባልተናነሰ መልኩ "በግለሰብ፣ በቤተሰብና በማህበረሰብ ላይ ከባድ ጫና እያደረሰ ያለ የጤና ችግር ነው"። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በሰው ኃይል ስልጠና ዓይነትና ብዛት እንዲሁም በአገልግሎቱ ስርጭት በኩል ለውጦች ቢኖሩም ከችግሩ ስፋት አንጻር ሲታይ ግን የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑን ነው የገለጹት። የአእምሮ ጤና ጉዳይ የጤና ዘርፍ ችግር ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሴክተሮችን ርብርብ የሚጠይቅ ባለብዙ ዘርፍ ችግር መሆኑንም ገልጸዋል። እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ እራስን በራስ የማጥፋት ድርጊት ከአዕምሮ ህመሞች አንዱ ሲሆን ማህበረሰቡ በአዕምሮ ህመም ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑም ችግሩን የበለጠ የተወሳሰበ አድርጎታል። እራሳቸውን ከሚያጠፉ አስር ሰዎች መካከል ዘጠኙ የአዕምሮ ህመምተኞች መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱም አክለዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችና ጎልማሶች እራስን ለማጥፋታቸው አንዱ ምክንያት በሆነው በድባቴ(Depression) የአዕምሮ ህመም ተጠቅተው ለህክምና ወደ ጤና ተቋማት እንደሚመጡ አንስተዋል። በመሆኑም የአዕምሮ ህክምና አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማሻሻልና በትብብር ለማከናወን የሚያስችል ብሄራዊ ስትራቴጂ ማዘጋጀትና መተግበር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር አታላይ አለም በአሁኑ የአገሪቱ ሕዝብ ብዛት ሲሰላ በተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች ሱስ የተቸገሩትን ጨምሮ ከ27 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የባለሙያ እገዛ የሚያስፈልገው የአእምሮ ህመም ያለበት ሕዝብ እንደሚኖር ጥናቶች ያመለክታሉ ብለዋል። በኢትዮጵያ የባህል ለውጥ መፋጠን፣ የሥራ አጥነት ብዛት፣ የከተሞችና የከተሜነት ኑሮ መስፋፋት፣ የአደንዛዥ ዕፆች አጠቃቀምና የአልኮል መጠጥ መስፋፋት መፈናቀልና አለመረጋጋት እንዲሁም ሌሎች ለአእምሮ ሕመም አጋላጭ ሁኔታዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። የአገልግሎቱ ተደራሽነት ውስንነት፣ የህክምና ግብዓቶች እጥረት፣ የመድኃኒቶች አቅርቦትና ውድነት እነዲሁም የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ድምጽ አልባነት ተግዳሮቶችንም ፕሮፌሰር አታላይ ጠቅሰዋል። የአእምሮ ሕመምተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን ማውጣት፣ መድኃኒቱ በነጻ እንዲደረስ ማድረግ፣ አጋላጭ ሁኔታዎች ላይ ትኩርት ሰጥቶ መስራት ደግሞ ከመፍትሄዎች መካከል አክለዋል። እንደ ፕሮፌሰር አታላይ ገለጻ በአገሪቷ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የአደገኛ ዕጾች አጠቃቀም ስርጭትን ለመግታት ሕግና ደንብ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። የአማኑኤል ስፔሻላይዘድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ኤዶ ፈጆ ራስን ማጥፋት ከ15 እስከ 29 አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ወጣቶች ሞት በ2ኛ ደረጃ መንስኤነት የሚጠቀስ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል። ይህ የሚያሳየው የአዕምሮ ህመም አምራች የሆነውን ወጣት ሀይል በመጉዳት በአገር ልማትና ዕድገት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን ነው ብለዋል። በመሆኑም ወጣቶችን ለአዕምሮ ህመም ተጋላጭ ከሚያደርጉ ነገሮች በመጠበቅና የአዕምሮ ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁ ስራዎችን በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል። በአለም በአመት ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን ያጠፋሉ፤ ይህም በየ40 ሰከንድ አንድ ሰው ይሞታል ማለት ነው። ከእነዚህ ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት በመካከለኛና በአነስተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገራት ይኖራሉ።