የካፋ ነገስታት መካነ መቃብር ለቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ተጠየቀ

ሚዛን ኢዜአ መስከረም 28/2012 ታሪካዊው የ18ቱ የካፋ ነገስታት መካነ መቃብር "ሾሻ ሞጎ" ለምቶና ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎለት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን የካፋ ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ። የካፋ ነገስታትን የሚዘክር ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታውቀዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል አቶ አሸብር ከበደ እንዳሉት በዞኑ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቢኖሩም አለመልማታቸውን ይገልፃሉ። የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሃብቶች ተገቢው የማስተዋወቅ ስራ ባለመከናወኑም መስህቦቹ እንዳይጎበኙ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በዞኑ ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ውስጥም የካፋ ነገስታት መካነ መቃብር ሾሻ ሞጎ አንዱ ነው ያሉት አቶ አሸብር ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠውም ተናግረዋል። ከዋናው መንገድ እስከ መካነ መቃብሩ የሚያደርሰው መንገድ አለመሰራቱ ጎብኝዎች በቀላሉ ገብተው እንዳይጎበኙ እንዳደረገም አስታውቀዋል፡፡ ''መካነ መቃብሩ 18ቱ የካፋ ነገስታት በክብር ያረፉበት ቦታ ቢሆንም ተገቢው እንክብካቤ አልተደረገለትም'' ያለው ደግሞ ወጣት መሀመድ እስማኤል ነው። ''ወጣቶች የአባቶችን ታሪክና ቅርስ እንዲያውቁ ታሪካዊ ቦታዎች ሊለሙና ለጉብኝት ምቹ ሊደረጉ ይገባልም'' ብሏል። መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ቢሟሉለትና ተገቢው የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራለት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡ አቶ አበባዬሁ አበበ በበኩላቸው 18ቱ የካፋ ነገስታት በክብር ያረፉበት ታሪካዊ ቦታ ከታሪካዊነቱ አንጻር ትኩረት አለማግኘቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል። ታሪካዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ ቅርሶችን የያዘ ቤተ መዘክር መገንባት እንደሚገባ ጠቁመው ለባህላዊ አስተዳደር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በማጉላት ሰፊ የጥናትና ምርምር ማዕከል ማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ የካፋ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስረስ አዳሮ ከነዋሪዎቹ የቀረበው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ገልፀው ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ከ1387 እስከ 1897 ዓም ያስተዳደሩት የካፋ ነገስታትን የሚዘክር ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንና በአጭር ጊዜ ወደተግባር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደሚገኙ የገለፁት ኃላፊው ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግና በተለያዩ አማራጮች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የካፌቾ ብሄር ዘመን መለወጫ የሆነው የማሽቃሬ ባሮ በስፍራው መከበሩ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም