በአፋር ክልል የተከሰተው የኮሌራ፣ ኩፍኝ እና ደንጉ በሽታዎችን የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የተከሰተው የኮሌራ፣ ኩፍኝ እና ደንጉ በሽታዎችን የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው
መስከረም 28/2012 በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በወረርሽኝ መልክ የተከሰተውን የኮሌራ ኩፍኝና ደንጉ በሽታዎችን የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ አብዱ አሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኩፍኝ በአፋምቦ፣ ዱብቲ ፣ አይሳኢታና ጉሊና ወረዳዎች ተከስቷል። ኮሌራ ደግሞ በእዋ ወረዳ እንዲሁም የደንጉ በሽታ በገዋኔ ከተያዘው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ እንዲሁ። ሆኖም ከአርብቶ አደሩ ተንቀሳቃሽ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች አንድ ግዜ መቀነስ ሌላ ጊዜ የሚጨምርበት ሁኔታ እንደሚስተዋል አስረድተዋል። ኩፍኝ በተከሰተባቸው ወረዳዎች ለመከላከል በተደረገው ጥረት እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም አልፎ አልፎ በሽታው የተጠቁ ሰዎች ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚመጡ አመልክተዋል። በቀጣይ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች ከሚሰጡ የህክምና አገልግሎት በተጓዳኝ በክልሉ በመደበኛ ፕሮግራም ከሚሰጠው የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ በዘመቻ መልክ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባት እየተሰጠ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ በተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ በገዋኔ ወረዳ በተከሰተው የደንጉ ወረርሽኝ እስካሁን 450 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ህክምና እንደተሰጣቸው ተመልክቷል። አስተባባሪው እንዳስረዱት ደንጉ " ኤዴስ " በምትባል የበሽታ አምጭ ትንኝ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ ከፍተኛ ትኩሳትና እራስ ምታት እንዲሁም የድካም ምልክት የሚያስከትል ነው። ምልክቱ የታየበት ሰው በጊዜው ህክምና ካላገኘ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል በሽታ እንደሆነ ነው የተገለጸው። በክልሉ በወረርሽኝ መልክ የተከሰቱት ሶስቱ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ስራ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስተባባሪው አብራርተዋል።