ቀጥታ፡

የጨለለቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ለዓመታት በመዘግየት በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል

ዲላ (ኢዜአ) መስከረም 28 / 2012 ዓ.ም በጌዴኦ ዞን ጨለለቅቱ ከተማ በ1 ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ግንባታው የተጀመረው ሆስፒታል ባለመጠናቀቁ የጨለለቅቱ ከተማና የኮቾሬ ወረዳ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል የጨለለቅቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ሲሳይ ብሩ የሆስፒታሉ ግንባታ ከአምስት ዓመት በፊት መጀመሩን አስታውሰዋል። በወቅቱ የግንባታ ሥራው ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ ሥራ ቢገባም እስከዛሬ ድረስ ሆስፒታሉ አለመገንባቱ ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸዋል፡፡ የጨለለቅቱ ከተማን ጨምሮ የኮቾሬ ወረዳና የአካባቢው ነዋሪዎች የተሻለ የጤና አገልግሎት ለማግኘት ሲሉ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ይርጋጨፌ ወይም ዲላ ከተሞች ለመሄድ መገደዳቸውንም ተናግረዋል። ይህም እሳቸውን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ከመዳረጉ ባለፈ ሲታመሙ ፈጣን የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡ አቶ ሲሳይ እንዳሉት ደረጃውን የጠበቀ የጤና ተቋም በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ በተለይ ነፍሰጡር እናቶችና አደጋ የደረሰባቸው ዜጎች ለከፋ ጉዳትና ለሞት እየተጋለጡ ነው፡፡ መንግስት የተቋረጠውን የሆስፒታል ግንባታ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስጀምሮ የህብረተሰቡን የተሻለ የጤና አገልግሎት ጥያቄ እንዲፈታም ጠይቀዋል፡፡ በኮቾሬ ወረዳ የባያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ታርኳ ፈይሳ በበኩላቸው "የጨለለቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ አለመጠናቀቅ ለተጨማሪ ወጭና እንግልት ዳርጎናል" ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን በአካባቢው ውስን የጤና ጣቢያዎች ቢኖሩም ከፍ ያለ ሕክምና የሚፈልጉ ሕሙማንን ለማከም የግብዓትና የሰው ኃይል እጥረት እንደሚስተዋልባቸው ተናግረዋል። "በእዚህም የወረዳውና የአካባቢው ነዋሪዎች የጤና እክል ሲገጥመን የተሻለ የጤና ተቋም ፍለጋ ለተጨማሪ ወጭና እንግልት እየተጋለጥን ነው" ብለዋል፡፡ መንግስት ችግራችንን ተረድቶ የወረዳው ማዕከል በሆነችው ጨለለቅቱ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ቢያስጀምርም ሥራው መቋረጡ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። የጨለለቅቱ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈትቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ ከ5 ዓመት በፊት ግንባታው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ግንባታው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ቢታሰብም ከመሰረት ቁፋሮ ሳያልፍ ሥራው መቋረጡን ተናግረዋል፡፡ የሆስፒታሉ የግንባታ ሂደት መዘገየቱና መቆሙን በአካልና በጽሑፍ ለሚመለከታቸው የዞንና የክልል አካላት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም ምላሽ አለመገኘቱ አስረድተዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅሩ በደቻ በበኩላቸው የጨለለቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከክልሉ በተገኝ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማስገንባት ሥራው መጀመሩን ገልጸዋል። ለሆስፒታሉ በ2007ዓ.ም የቦታና የዲዛይን ዝግጅት ተደርጎ በ2009 ዓ.ም ወደ ግንበታ መገባቱን ገልጸዋል፡፡ ግንባታው ሲጀመር ስራው በ540 ቀናት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ቢባልም እስካሁን ድረስ አፈጻጸሙ ከ12 በመቶ አለማለፉን ጠቁመዋል፡፡ "ለግንባታ መዘግየቱ የሥራ ተቋራጬ በውሉ መሰረት ተግባሩን አለማከናወን ነው" ያሉት አቶ ፍቅሩ ማስተካካያ እንዲደረግ በተደጋጋም አቅጣጫ ቢቀመጥም ለመስራት ፍቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል። በእዚህም መምሪያው ከክልል ጤና ቢሮና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ውሉ እንዲቋረጥ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም የሆስፒታሉን ግንባታ ለማስጀምር አዲስ ጨረታ እንደሚወጣ አመልክተዋል፡፡ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ላማጎ በበኩላቸው "የግንባታ ቦታን ከይገባኛል ነጻ አድርጎ አለማቅረብ እና የተቋራጩ አቅም ማነስ የሆስፒታሉን ግንባታ አዘግይቶታል" ብለዋል፡፡ ተቋራጩ አፈጻጸሙን እንዲያስተካከል በተደጋጋሚ አቅጣጫ ቢቀመጥም "የግንባታ ግብዓት ዋጋ ጨምሯል" በሚል ምክንያት በውሉ መሰረት መስራት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ ቢሮ ውሉን ሙሉ በመሉ አቋርጦ ስራውን ለሌላ ሥራ ተቋራጭ ለማስተላለፍ የሰነድ ስራዎችን እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ የሆስፒታሉን ግንባታ እንደሚጀመር አመልክተዋል። የጨለለቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በወቅቱ ከ200 ሺህ በላይ ሕዝብን ያገለግላል ተብሎ ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም