ቀጥታ፡

ውህደቱ አሳታፊነትንና ባለቤትነትን በማጠናከር ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን ያሰፋል- አቶ አባተ ኪሾ

ኢዜአ፤ መስከረም 28/2012 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ውህደት ከሚያስገኘው ፋይዳ አንጻር የዘገየ ቢሆንም እጅግ ጠቃሚ ነው በማለት የቀድሞ የፓርቲው አባል ተናገሩ።

ፓርቲው ባለፈው ዓመት በሐዋሳ ባካሄደው ጉባኤ ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት አባልና አጋር ፓርቲዎቹን አዋህዶ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመሆን ሒደቱን ጀምሯል።

ውህደቱን በተመለከተ ኢዜአ ቀድሞ የደኢሕዴን አባልና የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ከነበሩት አቶ አባተ ኪሾ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አቶ አባተ ቀደም ሲልም አጋር ፓርቲዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህን መሰሉን ጥያቄ ያነሱ ነበር ብለዋል።

በዚህ ወቅት የውህደቱ አስፈላጊነት በምንም መልኩ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም የሚሉት አቶ አባተ ''አጋር ፓርቲዎች ከዳር ወደ መሐል እንዲመጡ ያደርጋቸዋል'' ይላሉ።

እነዚህ ፓርቲዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በትልልቅና ዋና ዋና አገራዊ ውሳኔዎች ላይ ሳይሳተፉ የውሳኔው ፈጻሚ እንዲሆኑ ይገደዱ ነበር ነው ያሉት።

ውህደቱ ከዚህ አንጻር አሳታፊነትንና ባለቤትነትን በማሳደግ ለዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ መስፋትና ለፌዴራል ስርዓቱ መጠናከር በጎ አስተዋዕኦ ያበረክታልም ብለዋል።

በተጨማሪም የፓርቲው ወደ ውህደት መምጣት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከ100 በላይ የሆኑት ፓርቲዎች እንዲዋሃዱም ምሳሌ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

ኢሕአዴግ ራሱ ሳይዋሃድ ሌሎቹን ተዋሃዱ ማለት ተገቢ አለመሆኑንና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲዋሃዱ በተግባር ለማሳየት እንደሚረዳም አቶ አባተ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ውህደቱ ሲፈጸም ከምንም በላይ ከዚህ በፊት የነበሩትን ክፍተቶችና ስህተቶችን በአግባቡ ማረም በሚያስችል መልኩ መሆን እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

በቀደሙት ጊዜያት ግንባሩ በፓርቲዎቹ መካከል የነበሩትን ያልተገቡ ግንኙነቶች ለማስተካከል የተለያዩ ተሃድሶዎችን ቢያደርግም ስኬታማ አልነበረም ብለዋል።

የአሁኑ የግንባሩ የውህደት እንቅስቃሴ የነበሩትን ችግሮች በተሻለ መልኩ መፍታት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም ከአራት ክልሎች በተውጣጡ አባል ፓርቲዎችና ከአምስት ክልሎች የተወከሉ አምስት ፓርቲዎችን በአጋርነት ይዞ የነበረ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም