ለሰላም ሁሉም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ የማይጨው ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ሁሉም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ የማይጨው ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ማይጨው (ኢዜአ) መስከረም 27 /2012 ዓ.ም በእንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለውን የሰላም እጦት ለመመለስ ህዝቡ በአንድነት መቆም እንዳለበት ኢዜአ ያነጋራቸው የማይጨው ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2012 የሥራ ዘመን የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮችና ለፌደሬሽን ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር ላይ ስለሰላም የተሰጠውን ትኩረት እንደሚደግፉትም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የአገሪቱን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ዜጎች በብሔር፣ በሃይማኖትና በፓለቲካ ሳይከፋፈሉ በአንድነት መቆም እንዳለባቸውም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት። የማይጨው ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት ደምሴ "ሰላማችን እያጣን ያለነው ራሳችን በምንፈጥራቸው የአስተሳሰብ ልዩነቶች ነው" ሲሉ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጸጥታ ኃይል ጥረት ሰላም ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ህዝቡ ያልተሳተፈበት ሰላም የማስፈን ሥራ ዘላቂ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። "ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አንድነቱን በማጠናከር የራሱን ሰላም በራሱ የመጠበቅ ሚናውን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል። "እርስ በርስ መግባባትና መደማመጥ እንዲኖር ቅድሚያ ሰላም ሊሰፍን ይገባል" ያሉት ደገሞ በጡረታ የሚተዳደሩት ኮማንደር ብርሃኑ ኃይሌ ናቸው። ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው በአንድነት የሚሰሩትን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ወንጀልን ለመከላከልና ወንጀለኛን ለህግ ለማቅረብም ስላም የማስፈኑ ሥራ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ጠቁመው መንግስት በዓመቱ ለሰላም ትኩረት መስጠቱን እንደሚደግፉት ተናግረዋል። "ማንም ህዝብ የሌላው ህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም፤ ይሁንና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ወደህብረተሰቡ በማስረጽ ህዝቡ ሰላሙን እንዲያጣ እየተደረገ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የማይጨው ከተማ ነዋሪ አቶ ገብረመድህን ካህሳይ ናቸው። ሕብረተሰቡ ፖለቲከኞች ሆን ብለው በሚፈጥሩለት አጀንዳ ሳይዘናጋ ለዘመናት ያዳበረውን አንድነት በማጠናከር ሰላሙን እንዲጠብቅ መክረዋል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሥህለወርቅ ዘውዴ "ሰላም በእያንዳንዳችን እጅና ልብ የሚገኘ ውድሀብት ነው" ያሉትን እሳቸውም ሆነ ማንም ሰላም ወዳድ ሰው እንደሚደግፈው ተናግረዋል።