ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ
መስከረም 27/2012 በኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ከአገር አልፈው ለዓለም ማቅረብ እንዲችሉ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ። የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለፈው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና በ2012 ዓም ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ተወያይቷል። በውይይቱ ላይ እንደተመለከተው የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ምርት ከውጭ ከሚገቡት መሰል ምርቶች ጋር ለመወዳደርና አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ምርቶችም ለመተካት እንደዚሁም ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ማዳበር ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ምርቶቻቸውን በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ማምረት እንዳለባቸው ነው የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳሙኤል ሐላላ የገለፁት። ይህንን እውን ለማድረግ የውስጥ የሰው ኃይል የማስፈፀም አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሳሙኤል "የምርት ጥራት የተረጋገጠለትን ምርት ወደ ገበያ ይዘን ካልገባን ተወዳዳሪነት የለም" ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመከላከል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የኢንቨስትመንት ትስስርን ለማጠናከርም ቅድሚያ ይሰጥ ብለዋል። በሥራ ላይ ከሚገኙት ኢንዱስትሪዎች መካከል ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን በማጥናት የብድር፣ የአቅም ግንባታና ሌሎች አስፈላጊ ማበረታቻዎች በቅድሚያ የሚመቻቹበት መንገድ እንዲዘየድም አሳስበዋል።