ቀጥታ፡

ከሐረር ከተማ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ መድኃኒቶች ተያዙ

አዲስ አበባ መስከረም  27/2012 --ከሐረር ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ወደመሀል አገር ሲዘዋወሩ የነበሩ የተለያዩ መድኃኒችን መያዙን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የኦፕሬሽን ኃይል አመራር የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ወንደሰን ካሳሁን እንደገለጹት ባለፉት ሳምንታት በህገ ወጥ መንገድ ወደመሀል አገር ሲጓጓዙ የነበሩ መድኃኒቶች የተያዙት በክልሉ ሐማሬሳ የመቆጣጠሪያ ስፍራ ነው። የጸጥታ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር በተደራጀ መልኩ ባከናወናቸው ሥራዎች ግምታቸው 100 ሺህ ብር የሚጠጋ የተለያዩ ህገ ወጥ መድኃኒቶች መያዛቸውን አመልክተዋል። በ21 የተለያዩ ካርቶኖች ተቀምጠው ሊተላለፉ ከነበሩ መድኃኒቶች መካከል በመርፌ፣ በደረቅና በፈሳሽ መልክ የሚወሰዱ የተለያዩ መድኃኒቶች እንዲሁም ሲሪንጅ ይገኙበታል። እንደ ምክትል ኢንስፔክተር ወንደሰን ገለጻ ከተያዙት መድኃኒቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው፣ ጥራታቸው ያልተረጋገጠና በጤናና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እውቅና ያልተሰጣቸው በርካታ መድኃኒቶች አሉ። በክልሉ የሚስተዋሉ ኮንትሮባንድ፣ ህገ ወጥ የመድኃኒት፣ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው በተለይ በወንጀል ድርጊቱ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ሕብረተሰቡም የአገርን ኢኮኖሚና ሰላም የሚገዳ ህገ ወጥ የኮንትሮባንድ፣ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲገጥመው ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን በጋራ የመከላከል ሥራውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም