ቀጥታ፡

ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን የልማት ኘሮጀክቶችን ለማገዝ ተዘጋጅቷል

መስከረም 27/2012 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ጥናት አጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት መዘጋጀቱን ገለጸ። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በደቡብ ሱዳን የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ እና በአገሪቷ የሥራ ጉብኝት ላይ ያደረጉትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኘሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊናን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። አቶ ባጫ ጊና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማገዝ በአገራቱ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል። ለዚህም ባንኩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ጥናት አጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ባንኩ ያቀዳቸውን የልማት ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤምባሲና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት የኢትዮጵያና የአገራቸው ወዳጅነት ከዲፕሎማሲያዊ የመንግስታት ትብብር ባሻገር በረጅም ሂደት የህዝብ ለህዝብ ትስስር የታገዘ መሆኑን አውስተዋል። ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ስላበረከተችው አስተዋፅኦና በሠላም ሂደቱ እየተጫወተች ስላለው ሚናም አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል የንግድ ትስስር ለመፍጠር አገራቱ በየብስ ትራንስፖርት መተሳሰር እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ደቡብ ሱዳን ወደ ኢኮኖሚ መልሶ ግንባታ እየተሸጋገረች በመሆኗ በተለይም የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ከኢትዮጵያ ለማስገባት በመንገድ ትራንስፖርት መገናኘት አስፈላጊ እንደሆነም ሳልቫኪር ተናግረዋል። አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮሙኒቲ አባላቱን በማስተባበር በደቡብ ሱዳን የልማት ስራዎች ንቁ ተሣትፎ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በዘርፈ ብዙ የልማት መስኮች በትብብር ለመስራት ከአሁን ቀደም የተለያዩ ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የደቡብ ሱዳን የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያትታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም