የአእምሯዊ ንብረትን ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ መገናኛ ብዙሃን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

96
አዳማ መስከረም  27/2012  የአእምሯዊ ንብረት እንደማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በንብረትነት እንዲታወቅ መገናኛ ብዙሃን በሕብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤን ለማሳደግ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ። የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት “የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች በማክበርና በማስከበር ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ሚና” በሚል ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል። በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ብሩክ ወርቅነህ እንዳስታወቁት በሀገሪቱ ጠንካራ አእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ከሰፈነ ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ የልማት መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በተለይ ለፈጠራ ስራዎች የሚደረገው ህጋዊ ጥበቃ ቀጣይ ለሚደረጉት የምርምር ስራዎች ተጨማሪ ሀብት በመሆን የኢኖቬሽን ሥርዓቱን ያሳድጋል ብለዋል። ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎች የኑሮ ሁኔታ በተሸለ ደረጃ ላይ እንዲቆም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በነጻ የገበያ ስርኣት ውስጥ በምርቶችና አገልግሎቶች መካከል መመሳሰልና መሳከርን ለማስቀረትና ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት ለመፍጠር እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን በሕብረተሰቡ ውስጥ የአእምሯዊ ንብረት ግንዛቤን ለማሳደግ አጀንዳ ቀርጸው በመስራት የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት ጽህፈት ቤቱ የሚያተኩርባቸው ዓበይት የአእምሯዊ ንብረት ዘርፎች የፈጠራ ባለቤትነት መብት ጥበቃና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ፣ የቅጂ መብትና የአእምሯዊ ንብረት ልማት መሆናቸውንም አቶ ብሩክ አስታውቀዋል። በእነዚህ ዘርፎች የሚፈልቁ የአእምሯዊ ንብረት እንደማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በንብረትነት የሚታወቁበትን አግባብ ለመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል። ለዚህ ስኬት ጽህፈት ቤቱ የተደራሽነት አድማስን ለማስፋት በባህር ዳር፣ ሀዋሳና ጅማ ከተሞች ቅርንጫፍ መክፈቱን ገልፀዋል፡፡ ከትግራይና ኦሮሚያ ክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲዎችም የአእምሯዊ ንብረት ዳይሬክቶሬቶች ተቋቁመው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በጽህፈት ቤቱ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃና ልማት ዳይሬክተር አቶ ናስር ኑር በበኩላቸው በሀገሪቱ የቅጅ መብት ጥሰት በአብዛኛው ከሚፈጸምባቸው ተቋማት መካከል የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ የማስታወቂያ ድርጅቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ሆቴሎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ካፌና ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛ ምሽት ክበባት፣ የሞባይል ጥገና ማዕከላት፤ ኢንተርኔት ካፌዎች፣ ቪዲዮና ሙዚቃ ቤቶች ሌሎቹ የቅጅ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው ናቸው። የቅጅና ተዛማጅ መብት ህጋዊ ተፈጻሚነት ላይ እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች ውሰጥ የህግ አስፈጻሚዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ ስለ ቅጅ መብት ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንን ጠቅሰዋል። በመሆኑም የወጡትን ህጐች ተፈፃሚ ለማድረግ የአቅም ግንባታ እና የግንዛቤ ማጐልበቻ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም