ቀጥታ፡

ካይዘን የሀብት ብክነት ከማዳን ባሻገር በአመራር ቁርጠኝነትና በሰራተኞች ተነሳሽነት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተገለጸ

አዳማ ሰኔ 9/2010 በሀገሪቱ  የካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ የሀብት ብክነት ከማዳን ባሻገር በአመራር ቁርጠኝነትና በሰራተኞች ተነሳሽነት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የገለጸ ። በካይዘን ላይ የተካሄዱ ሰባት የጥናትና ምርምር ውጤቶችና የስምንት ተቋማት ልምድ የሚቀርብበት የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል ። የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ በመድረኩ እንደተናገሩት ካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና ጥራትን ፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን ለማምጣት ፍቱን መሳሪያ ነው ። ፍልስፍናው ካይዘንን ተግባራዊ የሚያደርጉ ኩባኒያዎች ግብአትን ያልተጨመረበት የምርት ሒደትና ብክነትን በመቀነስ የጥራት ደረጃቸውን ማሻሻል እንደሚችሉ በጥናት ተረጋግጧል ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰራተኞች ላይ ተነሳሽነትን የሚያሳድግ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ገንቢ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ በጥራት ፣ በምርታማነትና በተወዳዳሪነት ላይ ጎልቶ የሚታይ ውጤት መታየት መጀመሩን አስረድተዋል ። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኮኮብ ደመቀ በበኩላቸው ካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና በሀገሪቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ 2 ቢሊዮን  600 ሚሊዮን  ብር የሚገመት ብክነት ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል። በተለያዩ ተቋማት እየተተገበረ ያለው ካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና የትግበራ ስፋቱን ፣መጠንና ውጤቱን ለመለካትና ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለይቶ ለመሙላት ሰባት የጥናትና የምርምር ስራዎች ተካሔደው ግኝታቸውን በዛሬው የምክክር መድረክ እንዲቀርቡ ተደርጓል። በተጨማሪ ስምንት  ኩባኒያዎች ልምዳቸውን ቀምረው እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን ነባራዊው እውነታው ከጥናትና ምርምር ውጤቱ ጋር ያለውን ተዛምዶ በጥልቀት በመፈተሽ ክፍተቶቹን ለመሙላት የሚያስችሉ የጋራ መግባባቶች ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል። በመድረኩ ካይዘንን በመተግበር ከሚገኙ 25 ኩባኒያዎች  ፣ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፣ ከክልሎችና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የተወጣጡና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከ100 በላይ የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው። ካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ከሚገኙ የለውጥ መሳሪዎች መካከል አንዱ ሲሆን በሙከራ ደረጃ 2002 እና 2003 ዓ.ም. ተተግብሮ ውጤታማ  በመሆኑ ከ2004 ዓ.ም. ወዲህ በሙሉ ትግበራ 500 በሚጠጉ ተቋማት ላይ እየተሰራበት ነው ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም