የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛ ኩባንያዎች ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛ ኩባንያዎች ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ መስከረም 27/2012 በተለያዩ የቴጅኖሎጂ መስኮች ላይ የተሰማሩ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ አነስተኛ ኩባንያዎች ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ። ኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎችም ልምድ ካካበቱ የአገረ ጃፓን ኩባንያዎችን ድጋፍ እንደሚሹ ገልጸዋል። ትናንት ማምሻውን 15 የጃፓን ኩባንያዎች ተወካዮች በተለያዩ ቴክኖሎጂ መስኮች ስራ ከፈጠሩ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ድርጅቶች ጋር በጃፓን ኤምባሲ ውይይት አድርገዋል። የቢዝነስ ልዑካኑ መሪ ኬን ሺቡሳዋ በተለይም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ልዑካኑ ከ51 አገሮች ከተውጣጡ ከ300 በላይ የኩባንያዎች ተወካዮች በሚታደሙበትና በአዲስ አበባ ለሚካሄደው በጤና ላይ ያተኮረ ምክክር መድረክ ለመሳተፍ 15 የቢዝነስ ድርጅቶች ተገኝተዋል። ኩባንያዎቹ እግረ መንገዳቸውን በኢትዮጵያ በተለያዩ ቴክኖሎጂ መስኮች ስራ ከሚፈጥሩ ኩባንያዎች ጋር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል። ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ለመጨመር በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑ ተናግረዋል። ከግብርና መስክ በተጨማሪ በጤና፣ በቆሻሻ አወጋገድና በሌሎች መስኮች ላይ ከአነስተኛ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር በትብብር መሰማራት እንደሚፈልጉ አረጋግጠዋል። በጋራ ውይይት መድረኩ የተለያዩ የፈጠራ ባለቤት የሆኑ አገር በቀል ኩባንያዎች ስለፈጠሩት ቴክኖሎጂ ምንነት፣ ፋይዳና ገበያ ሁኔታ በማስረዳት ከጃፓን ኩባንያዎች ጋር በትብብር መስራት የሚችሉባቸውን ጉዳዮች አስረድተዋል። አብዛኞቹ ኩባንያዎች ልምድ ካላቸው የጃፓን ኩባንያዎች የፋይናንስ፣ የሰው ሃይል አቅም ግንባታና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል። በተለያዩ ሰብዓዊ እርዳታና ለግብርና ስራዎች የሚያገለግል የድሮን ቴክኖሎጂ አምራች የሆነው 'ማይሻ ቴክኖሎጂስ' ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወጣት ትዝታ መንገሻ እንዳለችው፤ ማይሾ በኢትዮጵያ ብቸኛው ድሮን አምራች ኩባንያ ነው። ድሮን ከውጭ ማስገባት በህግ መከልከሉ ኩባንያቸው በገበያ በኩል መልካም እድል እንዳለው ገልጻ፤ ነገር ግን ድሮኑ ለሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት ቢውልም ከደህንነት ጋር ተያይዞ ያለው ቁጥጥር ለኩባንያው ተግዳሮት እንደሚሆን ነው የተናገረችው። ከ50 እስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚበሩ ሁለት አይነት የድሮን ቴክኖሎጂ ዲዛይን ማድረጉን ገልጻ፤ በማምረቻ ማሽን፣ የግብዓት፣ በአቅም ግንባታና በስራ ማስኬጃ ፋይናንስ መስኮች ልምድ ካላቸው የጃፓን ኩባንያዎች ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጻለች። በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ የሚሰራ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነው 'የኛ' የተሰኘውን ኩባንያ ወክላ የተገኘችው ሃና ጥላሁን ደግሞ፤ በጤና ጥበቃ ትኩረት በተደረገበት በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ መፍጠራቸውን ገልጻለች። ልምድ ያካበቱ የጃፓን ባንያዎችም በካፒታልና ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉና በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ አስረድታለች። ዘላቂነት ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱንጋ ገልጸዋል። አምባሳደሩ የጃፓን ኩባንያዎች በመደበኛነት ከሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ባሻገር በተለይም የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሚሰማሩባቸው እድሎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።