ቀጥታ፡

ለሰላማዊ የመማር ማስተማርና ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠቱን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) መስከረም 27 ቀን 2012 በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጠናከርና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ገለጸ። ማህበሩ "ወጣት መምህራን የሙያው አስቀጣይ ናቸው" በሚል መሪ ቃል የዓለም መምህራን ቀንን በአገር አቀፍ ደረጃ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አክብሯል። በበዓሉ ላይ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ እንደገለጹት በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን የሰላምና የአብሮነት ምሳሌ ማድረግ ይገባል። ትምህርት ያለ ሰላምና መረጋጋት እንደማይታሰብ ጠቅሰው፣ ማህበሩ ይህን ታሳቢ በማድረግም ባለፈው ዓመት ከ1 ሺህ 200 በላይ የትምህርት ሙያተኞች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፍረንስ ማካሄዱን አስታውሰዋል። በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴው እንዲጠናከር ማህበሩ በሰላም ጉዳይ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ዘንድሮም አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። እንደ ዶክተር ዮሐንስ ገለጻ መንግስት ከማህበሩ በጥናትና ምርምር የሚቀርቡለትን ሀሳቦችና የመምህራንን ጥያቄዎች በመቀበል ደረጃ በደረጃ እየፈታ ይገኛል። "የመምህራንን የሙያ ክብር ለማስመለስና በስልጠና አቅማቸውን በማጎልበት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ከሚደረጉ ጥረቶች በተጨማሪ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት በቅደም ተከተል እየተከናወኑ ይገኛል" ብለዋል። ብቃት ያላቸውና ሙያውን አጥብቀው የሚወዱ ወጣት መምህራንን በብዛት ለማፍራት ማህበሩ ከመንግስት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል። በተለይ የመምህራን የደረጃ እድገት መሻሻልና የመምህራን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በተሰራው ጠንካራ ስራ ከ54 ሺህ በላይ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት። የዓለም መምህራን ቀን መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ድምፃቸው እንዲሰማ የሚያደርጉበት እለት መሆኑን ጠቅሰው፣ በመድረኩ ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው በውይይት መዳበራቸውን ገልጸዋል። በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፋሽ ተካልኝ በበኩላቸው ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስኬት የአካባቢው ማህበረሰብና የመስተዳድር አካላት ሚና የላቀ ነው። ባለፈው ዓመት የአካባቢው ህዝብ ሰላማዊ የመማር ማስተማርን ለማስፈን የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውስው "ዘንድሮም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጋራ ሥራ ይሰራል "ብለዋል። በመንግስት በኩል አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደተግባር መሸጋገሩን የገለጹት ኃላፊዋ ፍኖተ ካርታው የመምህርነትን ሙያ የሚያፈቅሩ ወጣት ተመራማሪዎችን ለማፍራት አጋዥ መሆኑን ነው የጠቆሙት። ወደ መምህርነት ሙያ የሚመጡ ወጣቶች ለሙያው ፍቅር እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ አቶ ሞሲሳ ደጀኔ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስፈንና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አንድ የከፍተኛ ትምህርት የጥናትና ምርምር ማዕከል መደራጀቱን ተናግረዋል። የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለማሻሻል ከሙዋዕለ ህጻናት ጀምሮ ህፃናት ተኮትኩተው በእውቀትና በስነምግባራቸው የተሻሉ ሆነው እንዲወጡ መምህራን የድርሻቸውን እንዲወጡ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በበዓሉ ላይ በየደረጃው ያሉ የመምህራን ማህበር አባላትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወክለው የመጡ 250 የትምህርት ዘርፍ ሙያተኞች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም