ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የልዑካን ቡድን ነገ አዲስ አበባ ይገባል

መስከረም 27/2012 በ17ኛው የኳታር ዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፉ አትሌቶችና የልዑካን ቡድን አባላት ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ። ለአስር ቀናት በዶሃ ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት በተካሄዱ ወድድሮች ተጠናቋል። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለት ወርቅ፣ በአምስት ብርና በአንድ የነህስ ሜዳሊያ ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ከኬኒያ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት ውድድሩን አጠናቃለች። በውድድር የተካፈሉ አትሌቶችና የልዑካን ቡድን አባላት ነገ ጠዋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል ያደርጋሉ ተብሏል። በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ወይዘሮ ሳሚያ ዘከሪያ ለልዑካን ቡድኑ ትናንት ምሽት የእራት ግብዣ አድርገዋል። በዝግጅቱ ላይ የአትሌቲክስ ፌዴሬሸን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ በኳታር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለቡድኑ ለሰጡት ድጋፍ ምስጋና አቅርባለች። በሻምፒዮናው በወንዶች ማራቶን በአትሌት ሌሊሳ ደሲሳ የወርቅ፣ በአትሌት ሞስነት ገረመው የብር ሜዳሊያ ተገኝቷል። በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ሙክታር እንድሪስ የወርቅና ሰለሞን ባረጋ የብር ሜዳሊያ ያመጡ አትሌቶች ናቸው። በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ዮሚፍ ቀጀልቻ፤ በዚሁ ርቀት የሴቶች ውድድር ደግሞ ጉዳፍ ጸጋዬ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ለሜቻ ግርማ የብር ሜዳሊያ አስገኝተዋል። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ሶስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያ ያመጣች ሲሆን ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ስምንት ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም