ምክር ቤቱ የቤቶች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ፣ የከተማ መስፋፋትና መልሶ ማልማት ረቂቅ ስትራቴጂን አጸደቀ

82
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2010 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብንና የከተማ መስፋፋትና መልሶ ማልማት ረቂቅ ስትራቴጂን አጸደቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 49ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ ደንብና በከተማ መስፋፋትና መልሶ ማልማት ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል። ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከህንጻ ዕቃዎች አቅራቢ ድርጅት ጋር በመቀላቀል ኮርፖሬሽኑ ተወዳዳሪና ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ከማድረጉም ባሻገር በአቅርቦት እጥረትና የጥራት ችግር ምክንያት የሚስተጓጎሉ ስራዎችን ለመፍታት ያግዛል ተብሏል። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በከተማ መስፋፋትና መልሶ ማልማት ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የአገሪቱን ልማት ዘላቂና የተሳካ ለማድረግ የከተማ ልማት ስራ ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ አሰራርና አደረጃጀቶችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሻሻያና በየጊዜው ከሚኖረው ለውጥ ጋር የተጣጣመ ማድረግ ይጠይቃል ነው ያለው መግለጫው። የከተማ መልሶ ማልማትና ማስፋፋት ስራውን በተሳካ ሁኔታ መምራት፣ የአገሪቱን ዕድገት ቀጣይነት ባለው አስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባትና የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበታል። በመሆኑም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተማ መስፋፋትና መልሶ ማልማት ረቂቅ ስትራቴጂ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ማሻሻያዎች ታክለውበት በስራ ላይ እንዲውል ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም