ሴቶች ጠንካራ መንፈስ ከተላበሱ ካሰቡበት ለመድረስ የሚያግዳቸው የለም- ስኬታማ ሴቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች ጠንካራ መንፈስ ከተላበሱ ካሰቡበት ለመድረስ የሚያግዳቸው የለም- ስኬታማ ሴቶች
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2010 ሴቶች በስኬት ጉዞ ላይ ለሚገጥሟቸው ችግሮች እጅ መስጠት የለባቸውም ይላሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ስኬታማ ሴቶች። በኢትዮጵያ በርካታ ሴቶች በተሰማሩበት የሥራ መስኮች ስኬታማ በመሆን የአገራቸውንም ስም ጭምር በዓለም መድረክ ማስጠራት ችለዋል፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴቶች ተመሳሳይ የስኬት መስመር ላይ ይገኛሉ፤ ለአብነትም የፋሽን ዲዛይነር፣ የሞዴሊንግና የፋሽን ዲዛይን አስተማሪ እንዲሁም የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ መስራች፤ ዓለም አቀፍ ሞዴል ሣራ መሐመድ አንዷ ነች። ለሞዴሊንግ ካላት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ተማሪ ሆና የጀመረችውን ሙያ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ሞዴል ከመሆን አልፋ ኔክስት የተሰኘውን የሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ለማቋቋም መቻሏን ትናገራለች። እዚህ ለመድረስ የተለያዩ ውጣውረዶችን አልፋ ለስኬት መብቃቷን የገለጸችው ሞዴል ሣራ ሴቶች ለዓላማቸው መሳካት የሚገጥሟቸውን ችግሮች በብቃት ማለፍ ይገባቸዋል ትላለች። ሌላኛዋ ስኬታማ ሴት የእናት ባንክ መስራች ወይዘሮ አስካለ በንቲ በበኩላቸው ሴቶች ያለሙትን ለማግኘት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ይናገራሉ። በተለይም የሴቶች ፎረሞችና የትስስር መድረኮች ሴቶች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙና ልምድ እንዲቀምሩ በማድረግ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል። የአማሮ ጋዮ ቡና እንዲሁም የቦኒ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት ወይዘሮ አስናቀች ቶማስም ሴቶች ስኬታማ ለመሆን የሚያግዳቸው ነገር የለም ይላሉ። ይሁንና ሴቶች ዓላማቸውን ለማሳካት በትጋት መሥራትና እርስ በእርስም በመረዳዳት ከራሳቸው አልፈው ለአገራቸውም ውለታ መዋል እንደሚችሉ ነው የገለጹት።