ከሐረር ወደ ጅግጅጋ የሚወስደው የተሽከርካሪ መንገድ ድልድይ ተበላሽቶ አገልግሎት መቋረጡ ተገለጸ

99
ሐረር መስከረም 26/2012 ከሐረር ወደ ጅግጅጋ የሚወስደው የተሽከርካሪ መንገድ ኤረር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ላይ የሚገኘው የመተላለፊያ ድልድይ ተበላሽቶ አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን አሽከርካሪዎች ገለጸ። ከከባድ መኪና አሽርካሪዎች መካከል አቶ ደረጀ የማነህ  ለኢዜአ እንዳሉት ከድሬዳዋ ወደ ጎዲ የእርዳታ እህል ጭነው  እየተጓዘ ሳለ በመንገዱ መበላሸት ምክንያት በአካባቢው ለመቆም ተገደዋል። ድልድዩ  ተሰንጥቆ በወቅቱ ባለመጠገኑ  የጫኑትን የእርዳታ እህል ለሳምንት ያህል አለማራገፋቸውን  ተናግረዋል። በአካባቢውም የተደራጀ ጥበቃ ባለመኖሩ ንብረቱ ለዘረፋና ተሽከርካሪዎችም ለማለፍ ሲሞክሩ ለአደጋ መጋለጣቸውን ጠቁመዋል። የምግብና ውሃ አቅርቦት በአካባቢው ባለመኖሩ መቸገራቸውን ጠቅሰው የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። "ተለዋጭ መንገዱን  በአግባቡ ሰርቶ የሚያሳልፈን አካል በማጣታችን የያዝነውን ጭነት ሳናራግፍ በስፍራው ለመቆም ተገደናል" ያሉት ደግሞ የነዳጅ ቦቴ አሽከርካሪው አቶ መኮንን ቦጋለ ናቸው። በዚህም ምክንያት ለቀናት በመንገላታት ከጅቡቲ ድረስ ተጉዘው ለህዝብ ማድረስ የሚገባቸውን  ንብረት ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ አመልክተዋል። "በርካታ ስፍራዎች ላይ የመንገድ ብልሽት ያጋጥማል ይህን ከልምድ መመልከት ችያለው ወድያውኑ መፍትሄ ሲሰጥ ነው የምናየው ይህ ግን ሁሉንም እያማረረ ስለሚገኝ መፍትሄ ይሰጥበት "ብለዋል። ሌላው የከባድ መኪና አሽከርካሪው አቶ ሲሳይ ጌታቸው በበኩላቸው ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየስፍራውና ሐረር ከተማ ላይ በመቆማቸው የነዳጅ ዋጋ ጅግጅጋና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች ዋጋው በእጥፍ መጨመሩን  ተናግረዋል። መንግስት በጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ድልድዩ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። መፍትሄ ይገኛል በማለት በአካባቢውና ሐረር ከተማ ያለ ስራ በመቀመጥ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውንም አመልክተዋል። በድልድዩ መበላሸት  ምክንያት ከተሽከርካሪ ወደ ሌላ ተሽከርካሪ በቅብብሎሽ ሲጓዙ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ሁሴንለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል። " የትራንስፖርትታሪፍ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል ፤ በቅብብሎሽም ትራንስፖርት እየተጓጓዝ እንገኛለን "ብለዋል። መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የድሬዳዋ ዲስትሪክት ዳይሬክተር ኢንጅነር ሱራፌል ሚካኤል ስለጉዳዩ የኢዜአ ሪፖርተር በስልክ ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ "ከአራት ቀናት በፊት በስፍራው የነበሩትን ተሽከርካሪዎች በተለዋጩ መንገድ  ወደ ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬዳዋ እንዲተላለፉ አድርገናል" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በቦታው የሚገኙት ከዚያ ወዲህ  የገቡ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንደሆኑ አመልክተዋል። በአጭር ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ቢሰሩም የዝናቡ ሁኔታ በተለይ ደግሞ የአሽከርካሪዎች ትግስት ማጣት ተለዋጭ መንገዱን ይበልጥ ለተጨማሪ ብልሽት እየዳረገው መሆኑን ጠቁመዋል። "ዋናውን መንገድ በመዝጋት የኮንቦልቻ ጃርሶና ጭናክሰን መስመር  እንደአማራጭ አሽከርካሪዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ በሁለት ቀናት ውስጥ ተለዋጭ መንገዱን ለመስራት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም