"የውጭ ግንኙነት መርሃችን ፉክክርና ትብብርን ባማከለ መልኩ እንዲከናወን ታስቧል" - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ - ኢዜአ አማርኛ
"የውጭ ግንኙነት መርሃችን ፉክክርና ትብብርን ባማከለ መልኩ እንዲከናወን ታስቧል" - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ
መስከረም 26/2012 የውጭ ግንኙነት መርህ ፉክክርና ትብብርን ባማከለ መልኩ ለማከናወን መታሰቡን ፕሬዘደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። "በ21ኛው ክፍለዘመን ተወዳዳሪብቻ ሳይሆን አሸናፊ ሆኖ መውጣትም ያስፈልጋል" ያሉት ፕሬዚዳንቷ "ለዚህ ደግሞ የውጭ ግንኙነታችን በውስጥ ጥንካሬያችን ላይ ይወሰናል" ብለዋል። "ጠንካራ አንድነት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ስርዓትና ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ሲኖረን የውጭ ግንኙነታችንም በዚያው ልክ ጠንካራ ይሆናል ነው" ያሉት። በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውንም አንስተዋል። መንግስት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን መከተል በመቻሉ በተለያዩ የውጭ አገራት በእስርና በእግልት ላይ የነበሩ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል። ከጎረቤት አገራት ጋር በተፈጠረ መልካም ግንኙነት በተለይ ከኤርትራ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የአየር ትራንስፖርት ከመጀመሩም ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በህጋዊ ማዕቀፎች እንዲመራ ለማድረግ ድርድር እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከጎረቤትና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚያዊ ጥምረት ለመፍጠር የሚያግዙ የነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቶችና ያለ ቪዛ ወደ አገር ውስጥ መግባትን በመፍቀድ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነም ተናግረዋል። በሌላ በኩል በሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን ግንኙነት መስኮች በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ግንኙነትን የማጠናከርና ከአዳዲስ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመርም ተችሏል። በተያዘው ዓመትም የውጭ ግንኙነቱ በተለያዩ መሰረታዊ እሳቤዎች የሚመራ መሆኑን አብራርተዋል። ይህም ከዚህ ቀደም በውጭ ግንኙነት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ማሳደግ፣ የመግባባትና የትብብር መርህ ላይ መመስረት እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ይሆናል ነው ያሉት። ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ ፖሊሲ መከተል፣ የውጭ ግንኙነቶችን ብሄራዊ ክብርና የዜጎችን ክብር የሚያስጠብቅ እንዲሆን ማድረግም እንዲሁ። መንግስት ከጎረቤት አገራት እስከ ሩቅ ምስራቅና ምዕራብ አገራት ድረስ "የጋራ ጥቅማችንንና ክብራችንን ባስጠበቀ መልኩ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው" ሲሉም ተናግዋል።