የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መስከረም 26 ቀን 2012 በኢትዮጵያ የአግሮ ኢንዱስትሪውን ልማት ለማጠናከር ያግዛል የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ። ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ይፋ የሆነው ፕሮጀክቱ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል። የኢትዮጵያ መንግስት የኢንዱስትሪዉን ዘርፍ ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ ከ2010 ዓም ጀምሮ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ነው። ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚቆየው ፕሮጀክቱም የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚደግፍ ነው ተብሏል። ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ማስፈፀሚያም 78 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል። ከዚህም ዉስጥ 6 ነጥብ 1 ዶላር የሚሆነዉ ገንዘብ የሚሸፈነዉ በኢትዮጵያ መንግስት ነው። ቀሪዉ በአዉሮፓ ህብረት፤ በኮሪያ የወጪና ገቢ ባንክ፤ በአፍሪካ ልማት ባንክ፤ ኢግዊን በተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በሚገኝ ፋይናንስ ይሸፈናል ተብሏል። በአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ የቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብደሩ ካማራ በስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመሰረተ ልማትና የአቅም ግንባታ ለማሳደግ እንደዚሁም የአስተዳደር ተግባራትን ለማጠናከር ያግዛል። ከዚህም ሌላ ፕሮጀክቱ ለኢንዱስትሪዉ በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጠንካራ ሰንሰለት ለመፍጠርም ዓይነተኛ መሳሪያ ይሆናል ብለዋል። በዚህ ረገድም አርሶ አደሩና የህብረት ስራ ማህበራት የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸዉ ለማድረግ ፕሮጀክቱ ያግዛል ሲሉም ዶክተር ካማራ ተናግረዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ በጤና፣ በግብርናና በሌሎች ልማቶች ድጋፍ ሲያደርግ መቆይቱን አውስተዋል። ባንኩ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ግቡን እሰኪመታ ድረስም የገንዘብ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። አዉሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ሉኡካን ቡድን ጽህፈት ቤት የልማት ትብብር ኃላፊ ሚስተር ኤሪክ ሀብርት በበኩላቸዉ ፕሮጀክቱ በአራቱ ክልሎች የሚካሄደዉን የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ እየተደረገ ላለው ጥረት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የንግድና አንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትልወርቅ ገብረ እግዚያብሄር የኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ገና በጅምር ላይ የሚገኝና ብዙ ማነቆዎች ያሉበት እንደሆነ ጠቅሰው የእዉቀት፣ የክህሎት፣የፕሮጀክት አፈፃፀምና አስተዳደር ድክመት፤ የበጀት እጥርት፤ የኃይል አቅርቦትና በቂ የሆነ መሰረተልማት አለመኖር ዋነኛዎቹ የዘርፉ ችግሮች ናቸዉ ብለዋል። ፕሮጀክቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚበረክት በመጠቆም። ፕሮጀክቱ በተቀናጀ መልኩ እንዲመራ፣ አርሶ አደሩና የህብረት ስራ ማህበራትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተዉ መስራት እንደሚገባቸዉም አሳስበዋል።