ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ወልድያ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2010 በ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ወልድያ ከተማን 2 ለ 0 አሸነፈ። ዛሬ 4:00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በፍጹም ቅጣት ምትና በጨዋታ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ነው ጅማ አባ ጅፋር አሸናፊ መሆን የቻለው። በዚህም መሰረት ጅማ አባ ጅፋር ነጥቡን ወደ 48 ከፍ በማድረግ ለዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ ያጠናከረ ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ ወልድያ ከተማ መውረዱን አረጋግጧል። በተመሳሳይ ሰዓት ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ ከሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከተማ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በሌላ በኩል ዛሬ አዋሳ ላይ አዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በቦዲቲ ወላይታ ዲቻና ውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰኑ ቀናት መራዘሙ ተገልጾ የነበረ ሲሆን ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበትን ቀንና ሰዓት የፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ በመጪው ሰኞ በሚያደርገው ስብሰባ የሚያስታውቅ ይሆናል። በተጨማሪም ከቀናት በፊት በደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ህልፈተ ህይወት ምክንያት ለሌላ ቀን ተራዝሞ የነበረውን የደደቢትና አርባምንጭ ጨዋታ የሚካሄድበት ቀንም ይፋ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው። ዛሬ ከቀኑ በ11:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ፕሪሚየር ሊጉን ጅማ አባ ጅፋር በ48 ነጥብ ሲመራ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ45 ነጥብ ሁለተኛ፤ ኢትዮጵያ ቡናና መቀሌ ከተማ በተመሳሳይ 43 ነጥብ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባ ጅፋሩ ኦኪኪ አፎላቢ በ18 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም