ሁለገቡ የሙዚቃ ባለሙያ ኤልያስ መልካ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለገቡ የሙዚቃ ባለሙያ ኤልያስ መልካ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
መስከረም 26/2012 ሁለገቡ የሙዚቃ ባለሙያ ኤልያስ መልካ ስርዓተ ቀብር በጴጥሮስ ወ-ጳውሎስ ቤተክርስቲያን በሚገኘው የፕሮቴንታንት የመቃብር ስፍራ ተፈጽሟል። የአርቲስቱ ስርዓተ ቀብር ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል። ኤልያስ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ ጊታሪስት፣ ፒያኒስት ሲሆን፥ አዳዲስ ሙዚቀኞችን በማስተዋወቅ ይታወቃል። ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቼሎ የሙዚቃ መሳሪያን ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ከመምህሩ አክሊሉ ዘውዴ፣ ከእዝራ አባተና ከያሬድ ተፈራና ከሌሎችም ጋር በመሆን በመዲና ባንድ ውስጥ ሰርቷል። ከ30 በላይ ሙሉ አልበሞችን ልዩ አድርጎ ያቀናበረው ኤሊያስ መልካ፤ በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሆኑ ድምጻውያን እስከ አዳዲስ ድምጻውያን ጋር በርካታ ሙዚቃ በመስራት ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ አንጋፋ እና ወጣት የጥበብ ባለሙያዎች፣ ቤተሰቡ፣ የሙዚቃ አፍቃሪያን እንዲሁም በያሬድ ትምህርት ቤት ያስተማሩት መምህራን እና ሌሎችም ተገኝተዋል። ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ ባሳለፍነው ቅዳሜ ረፋድ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም በስኳርና በኩላሊት ህመም ምክንያት ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው። የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ጊታሪስት የሆነው ኤልያስ መልካ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያኖረ አርቲስት ነበር።