የወሎን መቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት እንደሚሰራ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የወሎን መቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት እንደሚሰራ ተገለጸ
ደሴ ኢዜአ መስከረም 26/2012 የወሎን ፍቅር ፣ መቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት እንደሚሰራ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ ገለጹ፡፡ በአካባቢው እያጋጠመ ያለውን የሰላም መታጣት ችግር መፍታት በሚቻልበት ዙሪያ በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው። ከክልልና ፌደራል መንግስት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ባለው መድረክ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ እንዳሉት የህግ የበላይነት ማስከበር ስራው ልማቱን እያጓተተ ነው። ህብረተሰቡም ፈጣን አገልግሎት እንዳያገኝ በማድረጉ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሯል። "ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልም በየመድረኩ በውይይት ብቻ ጊዜ ከማጥፋት ተቆጥበን ውጤት ለማምጣት አመራሩ ቁርጠኛ መሆን አለበት" ብለዋል፡፡ በደቡብ ወሎ የጸጥታ ችግር እንዲከሰት ጥቅመኞች ከፍተኛ ጥረትና ጫና ፈጥረው እንደነበር ያመለከቱት አቶ ሰይድ በተከናወነው ቅንጅታዊ ስራ ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ህገ ወጥ የቤት ግንባታ፣ ንግድና የጦር መሳሪያ ዝውውር ለማስቆም የተቋቋመው ግብር ኃይል ውጤት ማምጣቱን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም የወሎን ፍቅር፣ መቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ከአጎራባቾቻቸው ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ "ሰላማችንን በመጠበቅ ኢኮኖሚው እንዲጎለብት በስራ እድል ፈጠራና ግብርና ዘርፉ ላይ እናተኩራለን" ብለዋል፡ በየደረጃው ያለው አመራር ተጠናክሮ መንግስት የጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ማጎልበት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ የወረኢሉ ወረዳ ጸጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሌኤክ አሊ ናቸው፡፡ ለውጡን ተከትሎ በወረዳው ተፈጥሮ የነበረው ህገ ወጥ አካሄድ በየደረጃው በተደረገው ውይይትና ህግ የማስከበር ስራ ችግሩን በማቃለል ስርዓት መያዙን አስረድተዋል። በምክክር መድረኩ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው የህግ የበላይነትን በማስክበር የህብረተሰቡን የሰላምና የፍትህ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። "ለውጡን በማይደግፉ ኃይሎች በሚደረግ ድጋፍ በሚፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ አመራሩ ከመደበኛ የልማት ስራው በመውጣት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲጠመድ ተደርጓል "ብለዋል። በሀገሪቱ እያጋጠመ ያለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት የህግ የበላይነትን በማስከበር ወደ መደበኛ የልማት ስራው ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። የህብረተሰቡን የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶቹን በመሸርሸር ወደ ጥፋት የሚገፋፉ ማህበራዊ ሚዲያዎችና መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ "በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሰፍኖ የኖረውን ሰላም፣ ፍቅር፣ መቻቻልና አብሮነት ለትውልዱ እንዲተላለፍ አባቶችና ምሁራን ከወገንተኝት ጸድተው ስለሰላምና ደህንነት ማስተማር ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡ በመድረኩ በደቡብ ወሎ ዞን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ከክልልና ፌደራል መንግስት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡