ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

54
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2010 በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የአስተዳደር ወሰን ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል ሁሉን አሳታፊ ኮሚሽን ሊቋቋም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ምሽት መግለጫ ሰጥተዋል። የሚቋቋመው ኮሚሽን ከየአካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎችን በመቀበል ስር-ነቀል መፍትሔ ይሰጣል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በአንዳንድ አከባቢዎች በተለይም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሀዋሳ፣ ወላይታ፣ ወልቂጤና ሌሎች አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት  ክልሉን የማይገልጽና ሰላምን በማይፈልጉ ኃይሎች የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። የኃይማኖት እና የብሔር ልዩነቶችን ተጠቅመው ችግር ሊፈጥሩ ለሚፈልጉ ኃይሎች ህብረተሰቡ ዕድል እንዳይሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳስበዋል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚታወቅበትን የአብሮነትና የፍቅር ኑሮ የሚያደፈርስ፣ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጭና የሚያለያይ ተግባር የማያስፈልግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶና ወልቂጤ ከተሞች የተነሱትን ግጭቶችን ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ለመፍታት በቀጣዩ ሳምንት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ተገኝተው ከህዝቡ ጋር ውይይት እስኪያደርጉ  የትንሿ ኢትዮጵያ ማሳያ የሆነችው የደቡብ ክልል ነዋሪዎች፣ የአከባቢው ሽማግሌዎችና ወጣቶች ለአካባቢያቸው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም