ጦሳ ተራራን አልምቶ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ጦሳ ተራራን አልምቶ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ
ደሴ (ኢዜአ) መስከረም 26 ቀን 2012ዓ.ም----በደሴ ከተማ የሚገኘውን የጦሳ ተራራ በማልማትና በማስተዋወቅ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን እንደሚወጣ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ። "ጦሳን በፍቅር መውጣት ለጤንነት" በሚል መሪ ቃል ከደሴ ከተማ ተነስቶ መዳረሻውን ጦሳ ተራራ ላይ ያደረገ የፍቅርና የሰላም ጉዞ ተካሂዷል። በእግር ጉዞው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዱኛ ይግዛው እንዳሉት በውጪው ዓለም ተራራ ላይ የመውጣት ስፖርታዊ እንቅስሴ የተለመደ ነው። የደሴ ከተማ ማህብረሰብ በአካባቢው የሚገኙ ተራሮችና የተፈጥሮ ሀብቶችን በእግሩ ተጉዞ በመጎብኘት ጤንነቱን ከመጠበቅ ባሻገር ጎብኚዎችን በማላመድ የመስህብ አማራጭ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል። በክልሉ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ትውልዱ አካባቢውንና ታሪኩን በማወቅ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ ኮሚሽኑ አባቢዎችን መሰረት ያደረገ የስፖርት ልማት ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። "የተፈጥሮዊ ሀብቶችን በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንዲሁም አንድነትን፣ ፍቅርና ሰላምን ለማጎልበት በሚደረገው ርብርብ ኮሚሽኑ የበኩሉን ይወጣል" ብለዋል። የደሴ ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማህደር አራጌ እንደገለጹት የጦሳ ተራራ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ በተራራ ላይ ለሚካሄድ የጉዞ ውድድር (አድቬንቸር) ተመራጭ ነው። የውጭ ተሞክሮን ወደ አገር ውስጥ በማምጣትም መነሻውን ደሴ ከተማ በሚገኘው ፒያሳ አደባባይ በማድረግ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን ተናግረዋል። በጉዞውም ከምስራቅ አማራ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት፣ የስፖርት ባለሙያዎች የደሴና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። "ጉዞው ደሴ የፍቅር፣ የሰላምና የአብሮነት ከተማ መሆኗን ከማጎልበት ባለፈ በጦሳ ተራራ ላይ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም ጉልህ ሚና አለው" ብለዋል፡፡ የቱሪስት መዳረሻነትቱን ለማረጋገጥም የከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰረተ ልማቶችን ለማሟለት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። በጦሳ ተራራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውን የፍቅርና የሰላም ጉዞ በየወሩ ለማድረግ መታቀዱን የተናገሩት አቶ ማህደር፣ ይህም ህብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በየጊዜው በማድረግ ጤንነቱን ለመጠበቅ እንደሚያግዘው ገልጸዋል። ከተሳታፊዎች መካከል በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመጡት የስፖርት ባለሙያ አቶ ዘላለም ታደሰ "በወሬ የሰማሁትን የደሴ ከተማ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌትነት ዛሬ በተግባር አረጋግጨዓለሁ" ብለዋል፡፡ የጦሳ ተራራ ተፈጥሮዊ አቀማመጥና የአየር ጸባዩ ለቱሪስት ምቹ በመሆኑ መንግስት አካባቢውን በማልማት የሥራ ዕድል መፍጠሪያና የገቢ ምንጭ ማስገኛ ሊያደርገው እንደሚገባ ጠቁመዋል። በቀጣይም ተሞክሮውን ወደ ዞናቸው በመውሰድ ተራሮች እንዲጎበኙና የህብረተሰቡ የዕርስ በዕርስ ግንኙነት እንዲጠናከር ለማድረግ የድርሻቸውን እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡ ከኮምቦልቻ ከተማ የመጣችው ተሳታፊ ወጣት ሱምያ ያሲን በበኩሏ የጦሳ ተፈጥሯዊ በአቅራቢያዋ ቢገኝም እስከዛሬ ወደተራራው ወጥታ አለመጎብኘቷ እንደቆጫት ገልጻለች፡፡ "በጉዞው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረጋችን ባለፈ አንድነታችንን፣ ፍቅራችንና ሰላማችንን ለማጎልበት ስለሚረዳ በቀጣይ በየወሩ በሚዘጋጀው ጉዞ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ" ብላለች፡፡ በዕለቱ በእግር ጉዞው የተሳተፉ አካላት በተራራው ላይ የተተከሉ ችግኞችን በመኮትኮትና ውሃ በማጠጣት ለአረንጓዴ ልማት ስትራተጂው የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥዋል፡፡ በፍቅርና በሰላም ጉዞ ከ2 ሺህ በለይ የሚገመቱ የደሴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች እንዲሁም ከምስራቅ አማራ የተውጣጡ የስፖርት ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ታውቋል።