የኢሬቻ በዓል ለቀጣዩ ትውልድ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ መንከባከብ ያስፈልጋል - የበዓሉ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል ለቀጣዩ ትውልድ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ መንከባከብ ያስፈልጋል - የበዓሉ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ መስከረም 19/2012 የኤሬቻ በዓል የሠላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል በመሆኑ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ የበዓሉ ተሳታፊዎች ገለጹ። በቢሾፍቱ የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። ''ከአባቶቻችን የተቀበልነውን በዓል ለዚህ ትውልድ አስረክበናል የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ተንከባክቦ ለመጪው ማስረከብ አለበት'' ሲሉ ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች ገለጹ። የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ቤኩማ አመንቴ ''ባህሉንና እሴቱን በጠበቀ መልኩ ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማሳለፍ አለብን'' ብለዋል። ባህላዊ አለባበስ እና እሴቱን በመጠበቅ እንዲቀጥልና የበለጠ እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በዓሉን በማክበር ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ጨመዳ ዋጋሪ አዲሱ ትውልድ በዓሉ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ከወቅቱ ጋር እያጣጣሙ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በፍቅር እና አንድነት ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ''ከዚህ በበለጠ ደረጃ ዘመናዊ እንዲሆንና በቅርስነት እንዲመዘገብ ሁሉም በአንድነት መተባበር አለበት'' ብለዋል። ወይዘሮ አሚና ሳዶ በበኩላቸው ''በተለይ ወጣቱ ትውልድ በዓሉን ለቀጣይ ማስረከብ አለበት'' ሲሉ ተናግረዋል። ''የኢሬቻ በዓል ለትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናል፣ በአንድነት ለወደፊት መቀጠል አለበት'' ብለዋል የበዓሉ ተሳታፊዎች ።