ቀጥታ፡

ሙያዊ ስነ ምግባር በማይጠብቁ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ተባለ

መስከረም 25 /2012 ዓም ኢዜአ  መንግስት የጋዜጠኝነት ሙያዊ ስነ ምግባርን ጠብቀው በማይሰሩ አንዳንድ ሚዲያዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራንና የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በሚዲያዎች አዘጋገብና የህብረተሰቡ እይታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ትናንት በባህርዳር ከተማ አካሔዷል ። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ተቋም የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ወይዘሮ ፍቅርተ አዱኛ በምክክር መድረኩ ላይ ባቀረቡት ጥናት ሚዲያዎች የማስተማር፣ መረጃ የመስጠትና የማዝናናት ሃላፊነት አለባቸው። መንግስት የሚዲያ ነጻነትን ለማስከበር 70 የሚሆኑ ራዲዮና 28 የቴሌቪዝን ጣቢያዎች ከብሮድካስት ባለስልጣን ፈቃድ አግኝተው መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ "አንዳንድ ሚዲያዎች ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠና ወገንተኝነትን የሚያሳዩ ዘገባዎችን በመስራት ብሄርን ከብሄርና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ዘገባ በነስራት ተግባር ላይ መሰማራታቸውን እያየን ነው" ብለዋል። መንግስት ዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት መርሆዎችን በተደጋጋሚ የሚጥሱ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ ካልወሰደ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ የሚኖረው እምነት እየላላ አገር ወደ ማጥፋት የሚሄድ በመሆኑ ቀድሞ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል። በባህርዳር ሃገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አባ መላከምህረት ፈለገ ጥበብ አንዱዓለም እንዳሉት ጋዜጠኞች ያዩትን እውነታ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማያያዝ ትክክለኛ ዘገባ መስራት አለባቸው። አሁን ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያላዩትንና ያልሰሙትን መረጃ ከህብረተሰቡና ከአገር ጥቅም አንጻር ሳይመዝኑ በመልቀቅ ያልተገባ ድርጊት የሚፈጽሙ ሚዲያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ፈቃድ ሲወስዱ በገቡት ውል መሰረት በማይሰሩት ላይ መንግስት ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ የህብረተሰቡንና የአገር አንድነትን የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። ቤተ ክርስቲያናቸውም ለሀገራቸንና ለዓለም ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን በጸሎትና ምዕመኑን በማስተማር ላይ በማተኮር ለሰላምና ደህንነት መጠበቅ የበኩሏን ድርሻ እንድትወጣ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣቶች ትክክለኛና ተጨባጭ ዘገባ የሚሰሩና የማይሰሩትን በመለየት በስሜት ከሚፈጠር ቀውስ እራሳቸውን እንዲቆጥቡ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት መልሰው ስንቴ ነው። መንግስት በወንድማማች ህዝቦች መካከል መለያየትን የሚፈጥሩ ዘገባዎች ላይ በሚያተኩሩ ሚዲያዎች እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁሞ ለተግባራዊነቱም አስፈላጊውን ትብብር እናደርጋለን ብሏል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው አሁን ያለው መንግስት ቀደም ሲል ተዘግቶ የነበረውን የሚዲያ ነጻነት ክፍት አድርጓል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ፣ የህትመትና የማህበራዊ ድህረ ገጽ ሚፈዲያዎች ተፈጥረው ለህብረተሰቡ መረጃን በማድረስ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አንዳንድ ሚዲያዎች የሚዲያ ነጻነት ህጉና የዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት መርሆውን በሚጻረር መልኩ በወገንተኝነትና ሚዛናዊነትን ባልጠበቀ መልኩ ዘገባ እየሰሩ እንደሚገኙ ተመልክተናል ብለዋል። ይህም በአገራችን የተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ ነጸብራቅ በመሆኑ በቀጥታ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ባለስልጣኑ ሚዲያዎችን በማስተማርና በመለወጥ ወደ ትክክለኛው መርህ እንዲመለሱ እየሰራ ነው። ይህን ለማሳካትም በሳይንሳዊ ጥናት በመመስረት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለእያንዳንዱ ሚዲያ ግበረ መልስ መስጠት የሚጀመር ሲሆን ማስተካከል በማይችሉት ላይ በቀጣይ መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ብለዋል። ለአንድ ቀን በተካሔደው የምክክር መድረክ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም