የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የሁለቱንም ሀገራት ህዝቦች ፈቃደኝነት ባካተተ መልኩ እንዲፈጸም ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የሁለቱንም ሀገራት ህዝቦች ፈቃደኝነት ባካተተ መልኩ እንዲፈጸም ተጠየቀ
መቀሌ ሰኔ 8/2010 የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጉዳይ የሁለቱንም አገራት ህዝቦች ፈቃደኝነት ባካተተ መልኩ እንዲፈፀም ተጠየቀ፡፡ በትግራይ ክልል የሚገኙ የሴቶች፣ የወጣቶችና የአርሶአደሮች ማህበራት ኃላፊዎች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሰላም መታጣት ተጎጂ የሚያደርገው ህዝቡን እንደሆነ ገልጸው ፤ሰላምን ለማስፈን ደግሞ የሰላሙ ባለቤት የሆነው ህዝብ ተሳትፎ ሊኖርበት እንደሚገባ ገልጸዋል። የትግራይ ወጣቶች ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ገብረመድህን ሃጎስ የተረጋጋ ሰላም ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሚያደርገው ወጣቱን እንደሆነ ገልጾ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጉዳይም ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መልኩ እንዲፈጸም ጠይቋል። የትግራይ ሴቶች ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ገነት አረፈ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ በድንበር አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ሀሳብ መደመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳይ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ በሚችል መልኩ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለሁለቱም አገራት ህዝቦች እድል በሚሰጥ መልኩ መታየት እንሚኖርበትም ጠይቀዋል።