በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባገኙት ክህሎት አገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የህግ ታራሚዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባገኙት ክህሎት አገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የህግ ታራሚዎች ገለጹ
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባገኙት የሙያ ክህሎት ቤተሰባቸውንና አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን በይቅርታ የተፈቱ የህግ ታራሚዎች ገለጹ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በእስር ላይ የነበሩ 304 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ዛሬ ወስነዋል። ታራሚዎቹ 'እንፈታለን' ብለው ተስፋ አድርገው ያልነበሩና መፈታታቸውን የማያውቁ በመሆናቸው ይቅርታ እንደተደረገላቸው ሲሰሙ ማመን አቅቷቸው ደስታና ድንጋጤ ያለው የተደበላለቀ ስሜት ነበራቸው። ኢዜአ ያነጋገራቸው ታራሚዎች የተደረገላቸው ይቅርታ ያልጠበቁት እንደነበር በመግለጽ መንግስትን አመስግነዋል። አቶ ውብእሸት ቢተው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት 25 አመት ቆይተዋል። መንግስት የሞት ፍርደኞችን ጨምሮ ለታራሚዎች ይቅርታ እያደረገ በመሆኑ እሳቸውም ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም 'ዛሬ እፈታለሁ' የሚል ግምት አልነበራቸው። በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በስራ አመራር፣ በእንጨት ስራ፣ ብረታብረት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሌሎች በተለያዩ ሙያዎች የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ቤተሰባቸውንና አገራቸውን ለመጥቀምና ራሳቸውን በስራ ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ የግንቦት 7 አባል አቶ ሙፍታ ሸምሰዲን የተደረገላቸው ይቅርታ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተብሎ የተደረገ እንደሆነ የሚያምኑ መሆኑን ገልጸዋል። በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የህግን የበላይነት መማራቸውን የሚናገሩት አቶ ሙፍታ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉም በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ሌሎች አስተያየት የሰጡ የህግ ታራሚዎችም በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የወንጀልን አስከፊነት፣ የህግ የበላይነትንና የተለያዩ ሙያዎችን በመማራቸው ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ አረአያ በመሆን የወንጀልን አስከፊነት በማስተማርና በማገልገል ህብረተሰቡን ለመካስ መዘጋጀታቸውን ነው የሚናገሩት። ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ የሆነው ኬንያዊ ዊልሰን ጀድሩ የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገለት ምህረት ምስጋና አቅርቧል። በይቅርታ የተለቀቁት ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙና ራሳቸውን ለመለወጥ የተዘጋጁ መሆናቸው ተረጋግጧል። በይቅርታ ከተለቀቁ 304 ታራሚዎቹ ውስጥ 289 በሽብር ወንጀል፣ 3 በልዩ ልዩ ወንጀል ተከሰው የእድሜ ልክ እስረኛ የነበሩና መንግስት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው የጠየቁ፣ 9 የሞት ፍርድ የተወሰነባቸውና 3 የኬንያ ዜጎች ናቸው። መንግስት ለታራሚዎች ያደረገው ይቅርታ በህዝቦች ዘንድ ይቅርባይነት እንዲሰፍንና ባህል እንዲጎለብት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይበት እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጠቅሷል። ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ ክልሎችም በተመሳሳይ ይቅርታ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።