ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን የወርቅና የብር ሜዳሊያ አገኘች

73
መስከረም 25/2012 ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች የማራቶን ውድድር የወርቅና የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች። በኳታር ዶሃ እየተካሄደ የሚገኘው 17 ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በሚደረጉ ውድድሮች ፍጻሜውን ያገኛል። በትናንቱ የዘጠነኛ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን፣ በ1 ሺህ 500 ሜትርና በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድሮች ተካፍላለች። በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ በአትሌት ሌሊሳ ደሲሳ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ በአትሌት ሞስነት ገረመው ደግሞ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችሏል። ሌላው ትናንት ምሽት የተደረገው በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ሶስተኛ በመሆን    የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችላለች። ሌላው ትናንት ምሽት በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት አትሌት ጸሀይ ገመቹ፣ ፋንቱ ወርቁና ሃዊ ፈይሳ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል። በዛሬው የውድድሩ የመጨረሻ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የምትካፈል ይሆናል። በዚህ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌት ሀጎስ ገብረህይወት፣ አንዱአምላከ በልሁና ዮሚፍ ቀጀልቻ የምትወክል ይሆናል። ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለፍጻሜ ማለፍ ያልቻሉበት የወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር ፍጻሜ በዛሬው እለት ይካሄዳል። ኢትዮጵያ እስካሁን ባሉ ቀናት በሁለት ወርቅ፣ አራት ብርና አንድ ነሀስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያ በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀምጥ ችላለች። የደረጃ ሰንጠረዡን አሜሪካ፣ ኬኒያ፣ ጃይማይካና ቻይና ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው እየመሩ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም