በጋምቤላ የአሣ ሀብቱን በዘመናዊ መንገድ ለማልማት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

82
ጋምቤላ (ኢዜአ) መስከረም 24 ቀን 2012 በጋምቤላ ክልል ያለውን ከፍተኛ የአሣ ሀብት በዘመናዊ መንገድ ለማልማት የሚያስችል ፕሮጀክት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይፋ ሆነ፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በፕሮጀክቱ ግንባታና ቅድመ ዝግጅት ሥራ ላይ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ትናንት ውይይት አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በክልሉ መንግስትና በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሦስትዮሽ ስምምነት መሆኑም በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በክር እንዳሉት ፕሮጀክቱ በክልሉ ያለውን ሰፊ የዓሣ ሀብት በዘመናዊ መልኩ በማምረት ክልሉ ብሎም አገሪቱ ከዘርፉ የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን የማድረግ ዓላማ አለው። "ፕሮጀክቱ በተለይም የአሣ ሀብቱን ከአመራረት፣ ከአጓጓዝና ከግብይት ሂደት እንዲሁም ከማከማቻና ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ምርቱን በጥራት ለመጠቀም ያስችላል" ብለዋል። የማቀነባበሪያ ማዕከሉም የዓሣን ምርት በዘመናዊ መልኩ ከማቀነባበር በተጨማሪ የዓሣ መፈልፈያ እና የምርምር ማዕከል እንደሚኖረው አቶ ጀማል ገልጸዋል፡፡ እንደእሳቸው ገለጻ የዓሣ ማቀነባበሪያው ወደ ትግበራ ሲገባ ከ4 ሺህ በላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ዘላቂ የዓሳ ሀብት ልማትን በማሳደግ በኩልም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ በሚቀርበው የዓሣ ምርት በዓመት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚታሰብም ነው ተገለጹት፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በክልሉ በአይነትም ሆነ በብዛት ከፍተኛ የአሣ ምርት ቢኖርም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልታገዘ በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ዘርፉን በማዘመን የክልሉን ህብረተሰብ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፣ የክልሉ ዓሣና እንስሳት ሀብት ቢሮ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ዘርፉን ለማዘመን በትጋት መስራት እንዳለባቸውም  አቶ ኡሞድ አስገንዝበዋል፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኘው የአልዌሮ ግድብ ከፍተኛ የአሣ ምርት ቢኖረውም ብዙም ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አኩቾች አጉዋ የተባሉ የጋምቤላ ነዋሪ ናቸው፡፡ በተለይም ዓሣው የሚመረተው በባህላዊ መንገድ በመሆኑ ጫጩቶቹ ሁሉ ሳይቀር የሚጠመዱበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል። የዓሣ ማቀነባበሪያ በአካባቢው መገንባታ ይህንን ችግር በመፍታት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የዓሣ ምርት ያላቸው የአልዌሮና የባሮ ወንዞችን ጨምሮ የተለያዩ ውሃማ አካላት ቢኖሩም የሚመረተው የዓሣ ምርት ከአንድ ከመቶው ያልበለጠ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም