የኢህአዴግ የውህደት አቅጣጫ የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንደሚያሳድግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢህአዴግ የውህደት አቅጣጫ የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንደሚያሳድግ ተገለጸ
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 24/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር/ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ለመዋሃድ የመጀመሩት እንቅስቃሴ የሃገሪቱን ፖለቲካ የአሳታፊነት ሚና ከፍ ያደርገዋል ሲሉ በአሶሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለጹ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሐብታሙ ታዬ እንዳሉት ኢህአዴግ የጀመረው የመዋሃድ ጥረት በራሱ በግንባሩ እና ያለ አግባብ አጋር ተብለው ሲጠሩ በቆዩ ፓርቲዎች ጭምር ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ነው። በተለይም የኢህአዴግን የፓለቲካ ፕሮግራም መሠረት አድርገው የሚሠሩ አጋር ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የውስኔ ሰጪነት ሚና የተገደበ እንደነበረም አስረድተዋል። ይህም በሃገራዊ ባለቤትነት ላይም ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየቱን አፈ-ጉባኤው ጠቁመዋል። ውህደቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ በይፋ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ብሎም በሃገሪቱን ህዝቦች ዘንድ በጎ ነገር ይዞ እንደሚመጣ እምነት እንደተጣለበትም አስታውቀዋል። በተለይም በሃገሪቱ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ብቃትን ብቻ ለተከተለ የአመራር ምደባ እንደሚረዳ ገልጸው የፌዴራል ሥርዓትን በበለጠ በማጠናከር በመንግስት እና በፓርቲ መካከል ያለውን የአሠራር መደበላለቅ እንደሚያስቀርም አስረድተዋል። "ፓርቲዎቹ የሚፈጽሙት ውህደት በፌዴራልና በክልል መንግስታት አስተዳደር ውስጥም ይደገማል በሚል በጥቂት አካላት የሚነሳው ጉዳዩን በጥልቀት ካለመረዳት የመነጨ ከመላምት የማይዘል ሃሳብ ነው" ብለዋል። "ሀገሪቱ የምትከተለው በህገ-መንግስት በተደነገገ ፌደራሊዝም ነው" ያሉት አቶ ሐብተሙ ይህም ግንባሩም ሆነ መንግስት በተሻለ ለውጡን ማስቀጠል እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ/ቤጉህዴፓ አባልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አብዱሠላም ሸንገል በበኩላቸው "የግንባሩ የውህደት እንቅስቃሴ በሃገሪቱ የተጠናከረ ማህበረሰብ በመገንባት ለውጡን ማስቀጠል ያስችላል"ብለዋል። እንዲሁም ፈተና ውስጥ የገባውን የሀገሪቱን አንድነት በማጠናከር የግንባሩን የተበታተነ አካሄድ የማቀናጀት ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል። ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ህገ-መንስታዊ መብታቸውን ሲተገብሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ አብዱሠላም ይህንን በማጠናከር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ውሳኔ ማስተላለፍ ከቻሉ ውህደቱ ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል። "ኢህአዴግ የጀመረው ውህደት የብሄረሰቦችን እሴት በመጨፍለቅ በሃይል ወደ አንድ የሚያመጣ አካሔድ ይከተላል የሚል እምነት የለኝም" ብለዋል። በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ተጠሪ አቶ ብሩ ደሲስ በበኩላቸው ኢህአዴግ የጀመረው ውህደት የሚበረታታ ቢሆንም ተፈጻሚነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። "ኢህአዴግ ከጀመረው የውህደት ጥረት በተቃራኒ በየክልሉ ከህግ ይልቅ በብሔር መሠረት ያደረገ አሠራር አለመወገዱ፣ ህገ-መንግስቱ መጤ እና ነባር ብሎ የሚከፋፍል መሆኑ ፣ አንድነትን የሚሰብኩ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁንም በኢህአዴግ ካድሬዎች የሚዋከቡ መሆኑና ከሌሎችንም ችግሮች አለመላቀቁን የስጋቱ ማሳያ ነው" ብለዋል።